
በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ዳግማዊ ቴዎድሮስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ እየተሰራ ያለውን ባለአራት ወለል ህንፃ ግንባታ በጥሩ ሁኔታ ለማስቀጠል ሁሉም አካል አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት ተመላከተ፡፡
በትምህር ቤቱ የቀድሞ ተማሪወችና በማህበረሰቡ ተሳትፎ እየተገነባ ያለው ባለአራት ወለል ሁለገብ ህንፃ በሚፈለገው አግባብ እንዲቀጥል ለማድረግ ሁሉም አካል አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት ተመላክቷል፡፡
በትምህር ቤቱ እየተገነባ ያለው ባለአራት ወለል ህንጻ ግንባታ ያለበት ሁኔታ በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር አስተባባሪወች፣ በሌሎች የስራ ሀላፊወችና በከተማ ምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ምልከታ ተደርጓል፡፡
በምልከታው ላይ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ እየበሩ አእምሮ እንዳሉት በዳግማዊ ቴዎድሮስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቀድሞ ተማሪወችና በሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ በትምህርት ቤቱ እየተገነባ ያለው ባለአራት ወለል ህንጻ በአሁኑ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው ግንባታውን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
የህንጻ ግንባታው በሚፈለገው አግባብ እንዲሰራ ለማድረግ ክትትልና እገዛ እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረው ግንባታውን በጥሩ ሁኔታ ለማስቀጠል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት ጠቁመው ሁላችንም ተጋግዘንና ተባብረን በመስራት የህንጻውን ግንባታ ዳር ማድረስ አለብን ብለዋል፡፡
በዳግማዊ ቴዎድሮስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተገነባ ያለው ህንጻ አሰሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ በፍርዱ ወጨፎ እንደተናገሩት በትምህርት ቤቱ እየተሰራ ያለው ባለ አራት ወለል ሁለገብ ህንጻ በቀድሞው የትምህርት ቤቱ ተማሪወች፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በሚኖሩ ወገኖች ድጋፍ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው የተለያዩ ድርጅቶችም የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን አውስተዋል፡፡
ለህንጻ ግንባታው ድጋፍ ቃል የተገባውን ገንዘብና ቁሳቁስ የሚያሰባስቡ እና ድጋፎችን የሚያስተባብሩ ኮሚቴወች በተለያዩ ከተሞች ተቋቁመው ስራዎችን እየሰሩ መሆናቸውንም ጠቁመው የህንጻ ግንባታውን በጥሩ ሁኔታ ለማስኬድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረው ሁላችንም ርብርብ በማድረግ የግንባታ ስራውን አጠናክረን ማስቀጠል አለብን ብለዋል፡፡
በትምህርት ቤቱ እየተገነባ ላለው ባለአራት ወለል ሁለገብ ህንጻ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ወገኖች የገንዘብና የሀሳብ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ በፍርዱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍልና ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን እንዳሉት በዳግማዊ ቴዎድሮስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በቀድሞው የትምህርት ቤቱ ተማሪወችና በሌሎችም አካላት ድጋፍና ትብብር እየተገነባ ያለውን ሁለገብ ህንጻ በጥሩ ሁኔታ ለማስቀጠል በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ወገኖችን በማነቃነቅ ርብርብ ማድረግ እንደሚስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጎንደር ዲስትሪክትና ደብረታበር ቅርንጫፍ የስራ መሪወችና ሰራተኞች ከደመወዛቸው በማዋጣት በቅርቡ ለህንጻው ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ በማድረጋቸውም አመስግነው ለሌሎቻችንም አርእያ የሚሆን ታላቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በከተመዋ ያሉትን ኮንትራክተሮችና ባለሀብቶች ለህንጻው ግንባታ ድጋፍ እንዲያደርጉ ማስተባበር እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ከንቲባው ሙያው ያላቸው አካላትም ሙያዊ እገዛ በማድረግ የህንጻውን ግንባታ በጥሩ አግባብ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ/ም
ለተጨማሪ መረጃዎችን በሌሎች የሚዲያ አማራጮች ይመልከቱ!
ፌስ-ቡክ፡-https://www.facebook.com/profile.php?id=100064645364506
ቴሌግራም ቻናል ፡- https://t.me/dtcommunication
ትዊተር፡- https://twitter.com/debre_tabor_com
ዩቲዩብ፡- https://youtu.be/BktVrGvXms
