የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከጠቅላላ አመራሩ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በወቅታዊ የሰላምና ፀጥታ ስራ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

በመድረኩ ላይ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሀብታሙ ጌታሁን ወቅታዊ ሁኔታውን አስመልክተው ሰነድ አቅርበዋል፡፡ በርካታ ጠላት ደብረታቦርን በመያዝ የሚፈልገውን እኩይ ድርጊት ለመፈፀም ቢመጣም በአመራሩ ቁርጠኝነት እና በሁሉም የፀጥታ ሀይል ተጋድሎ የጠላት ሀይል ትልቅ ኪሳራ ደርሶበት እና ተመትቶ መመለሱን ገልፀዋል፡፡ የከተመዋ ህዝብ እና በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖችም በተለያየ መንገድ እገዛ ማድረጋቸውን አንስተዋል ለጠላት የሚላላኩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ወደ ከተመዋ መጥቶ የነበረው የጠላት ሀይል የውጭ ጠላቶች ያደርጉታል ተብሎ በማይታሰብ ደረጃ የክፋት ጥግ የደረሰ ድርጊት መፈፀሙን ተናግረው ህጻናትንና ሴቶችን መድፈሩን፣ በመንግስት ተቋማት ሀብት ንብረት እና በግለሰብ ቤት ሀብት ንብረት ውድመትና ዘረፋ መፈፀሙንም ገልፀው የጥፋት ቡድኑ ያደረሰው ጉዳት ለህዝብ የማያስብ መሆኑን እና ዘራፊ እንደሆነ ማረጋገጫ ነው ብለዋል፡፡
ሀላፊው አያይዘውም ጠላት መቸም ቢሆን ክፉ ከማድረግ የሚመለስ ባለመሆኑ ሁለንተናዊ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ህብረተሰቡን ማንቃት እና የጠላት ሴልን መከታተል እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙ አካላትም በሰጡት ሀሳብ ብዛት ያለው የጠላት ሀይል ከተመዋን ለማውደም እና ህዝቡን ለማንገላታት ቢመጣም በአመራሩ የአላማ ጽናት እና በመላው የፀጥታ አካል ተጋድሎ የጠላት ሀይል ተመትቶ መመለሱን አንስተው በቀጣይም ጠላት ከጥፋት የሚቆጠብ ባለመሆኑ ሁለንተናዊ ዝግጅት ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡
የደብረታቦርን እና አካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ ከደቡብ ጎንደርና ከፋርጣ ወረዳ ጋር በጋራ መስራት እንደሚገባም ጠቁመው የጠላት ሴል የሆኑ ግለሰቦች ስላሉ በአግባቡ መተታልና እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ተናግረው ስራዎችን በተቀናጀና በተናበበ መንገድ መስራት አለብንም ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ደበበ አክሎግ እንደገለጹት ወደ ከተመዋ የመጣው የጠላት ሀይል በአመራሩ ቁርጠኝነት እና በፀጥታ አካሉ ቅንጅትና ተጋድሎ ተመትቶ መመለሱን አንስተው ህዝቡም ከመንግስት ጎን ሁኖ በተለያየ መንገድ ማገዙን ተናግረው ለመላው የፀጥታ አካል እና ለህዝቡ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በተካሄደው ጦርነት የተገኘው ድል ጠላት ላይ ትልቅ ቀውስ መፍጠሩን እና ለመንግስት ደግሞ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑንም ገልፀው በቀጣይም የጠላትን ሀይል አንገት ለማስደፋት በተጠናከረና በተደራጀ መንገድ መስራት እና ህዝቡን ማስተባበር አለብን ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን አንደተናገሩት የጠላት ሀይል በመንግስት ተቋማት ሀብት ንብረት እና በግለሰብ ቤት ሀብት ንብረት ውድመትና ዘረፋ ቢፈጽምም በነበረው የአመራሩ ቁርጠኝነት እና የፀጥታ አካሉ ተጋድሎ ተመትቶ መመለሱን አንስተው ህዝቡም ከመንግስት ጎን ሁኖ በተለያየ አግባብ እገዛ በማድረጉ አመስግነዋል፡፡
ጠላት እያደረገ ያለውን እኩይ ድርጊት በመረዳት የጠላት ሀይልን ለመዋጋት ሁለንተናዊ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበው ስራዎችን በቅንጅት መስራት፣ በአላማ ጽናት መታገል፣ በስነልቦና ከፍ ማለት እና የፀጥታ ሀይላችን ማጠናከር አለብንም ብለዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን የካቲት 12 ቀን 2018 ዓ/ም
