በደብረታቦር ከተማ እየተሰራ ያለው የገበያ ማረጋጋት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሀሳባቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ገበያውን ለማረጋጋት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን እና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ገልጿል፡፡
መንግስት ለሰራተኛው ያደረገውን የደመወዝ ጭማሪ እና ወቅታዊ ሁኔታውን እንደ ምክንያት በማድረግ በግብርና እና በኢንዱስትሪ ምርቶች እንዲሁም በሌሎችም እቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ተስተውሏል፡፡ ይህም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች እና ወርሀዊ ገቢ ባላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ችግር ፈጥሯል፡፡
ይህን ለማቃለልም መንግስት በተለያየ መንገድ የገበያ ማረጋጋት ስራ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ሀሳባቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ አቶ ክንዱ ደምሴ እና ወ/ሮ ያየሽ ድረስ በሰጡን አስተያየት እንዳሉት መንግስት ለሰራተኛው ካደረገው የደመወዝ ጭማሪ እና ከወቅታዊ ሁኔታው ጋር ተያይዞ በግብርና እና በኢንዱስትሪ ምርቶች እንዲሁም በሌሎችም እቃዎች ላይ የዋጋ መጨመር መኖሩን አንስተው መንግስት ገበያውን ለማረጋጋት እየሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ጤፍና ዘይት ለመንግስት ሰራተኛው በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ እየተደረገ መሆኑ ጥሩ እንደሆነም ጠቅሰው ለሌላውም የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ የሚሆንበት መንገድ መፈጠር እንዳለበት ጠቁመው ሌሎችንም የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ማቅረብ ቢቻል ገበያውን ለማረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልፀዋል፡፡
ነዋሪዎቹ አያይዘውም የንግዱ ማህበረሰብ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንደሌለበት ተናግረው ሸማቾቹም በሚፈጠሩ አሉባልታዎችና ትክክል ባልሆኑ መረጃዎች ከመሸበር ይልቅ ነገሮችን ቆም ብለን ማሰብ እና ከመስገብገብ መውጣት አለብን ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ታድሎ ድረስ እንደገለጹት ከወቅታዊ ሁኔታው እና ከደመወዝ ጭማሪው ጋር ተያይዞ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን እና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተው ባዛር እያዘጋጁ ሻጩን እና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት እንዲሁም በየሳምንቱ ሰባቱንም ቀናት የንግድ ልውውጥ እንዲኖር በማድረግ እና የግብይት ማእከላትን በማብዛት ገበያውን ለማረጋጋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በሰጠው የተዘዋዋሪ ብድርም የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት እንዲቀርብ በማድረግ ለመንግስት ሰራተኛው በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን እና በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው ሌሎችንም ምርቶች ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን እና ለሌላውም የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ የሚሆንበትን መንገድ ለማመቻቸት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ሀላፊው አክለውም ህገወጥ የንግድ ስራ በሚሰሩ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ጠቅሰው ነጋዴው ምክንያታዊ ካልሆነ የዋጋ መጨመር መቆጠብ እንዳለበት አሳስበው ሸማቹም ካለአግባብ የሚፈፀሙ ግብይቶችን ማካሄድ እንደሌለበት አስገንዝበው ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን ሲያይም መረጃ መስጠት አለበት ብለዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን የካቲት 10 ቀን 2018 ዓ/ም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top