የልማት ስራን በዘላቂነት ለመስራት ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ የሚያስፈልግ በመሆኑ ሁሉም አካል በባለቤትነት ይዞ ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የ2018 በጀት አመት የሰባት ወራት እቅድ አፈጻፀም በመገምገም የቀጣይ ቀሪ ወራት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በመድረኩ ላይ የመምሪያው እቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መብራቱ ገላው በተያዘው በጀት አመት ሰባት ወራት የተከናዎኑትን ተግባራት እቅድ አፈጻፀም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ የለውጥ ስራዎችን በአግባቡ ለማስኬድ መሰራቱን አንስተው ኢኮኖሚው የሚመነጨውን ገቢ በተገቢው ሁኔታ ለመሰብሰብም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በበጀት አመቱ 1 ቢሊየን 054 ሚሊየን 941 ሽህ 767 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በመደበኛ ገቢ 659 ሚሊየን 172 ሽህ 445 ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን እና በከተማ አገልግሎት ገቢ ደግሞ 395 ሚሊየን 769 ሽህ 322 ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቅሰው በሰባት ወራት ውስጥ 328 ሚሊየን 916 ሽህ 890 ብር የመደበኛ ገቢ መሰብሰቡን እና 100 ሚሊየን 106 ሽህ 656 ብር የከተማ አገልግሎት ገቢ መሰብሰቡን፤ በአጠቃላይ 429 ሚሊየን 023 ሽህ 546 ብር ገቢ በመሰብሰቡ የእቅዱ 40 ፐርሰንት ላይ መድረሱን አሳውቀዋል፡፡
የስራ ሂደት አስተባባሪው በቀጣይ ወራት የሚከናዎኑትን ተግባራትንም ያቀረቡ ሲሆን ገቢን በሚፈለገው አግባብ ለመሰብሰብ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ይዘው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበው የገቢ ስራ የሁሉንም ተቋማት ተቀናጅቶና ተባብሮ መስራት የሚጠይቅ በመሆኑ ሁላችንም በጋራ መስራት አለብን ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙ አካላትም በሰጡት ሀሳብ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን እና አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀው የሊዝ ክፍያን በተገቢው ሁኔታ ለመሰብሰብ በትኩረት ተይዞ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ለከተማው ትልቅ ገቢ የሚያስገኘው የመሬት ሊዝ ሽያጭ በመሆኑ ለሊዝ የሚቀርቡ መሬቶችን ለከተማው ቅርብ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመው ገቢ ሰብሳቢ የሆኑ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸውም ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ ሀላፊ አቶ ጌትነት ከቤ እንደገለጹት ገቢ ለአንድ ከተማና ሀገር ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ አንስተው የገቢ ስራን በጥሩ መንገድ ለማስኬድ ተቀናጅተንና ተጋግዘን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
በባለፉት ወራት ገቢን ለመሰብሰብ የተደረገው ጥረት አበረታች ቢሆንም በሚፈለገው አግባብ መፈፀም አለመቻሉን ጠቁመው ያሉትን ጥንካሬዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እና ክፍተቶቹን ደግሞ መሙላት እንደሚገባ አስገንዝበው ሁላችንም የገቢ ስራን በባለቤትነት ይዘን ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮነን እንደተናገሩት የአንድ ጠንካራ መንግስት መገለጫ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ እና ፀጥታን ማስከበር መሆኑን አንስተው የሀገር ኢኮኖሚ አስተማማኝ የሚሆነው በራስ አቅም በሚሰበሰብ ገቢ በመሆኑ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
እንደ ከተማ አስተዳደር ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ገቢን በመሰብሰብ ረገድ ሰፊ ችግር ያለ መሆኑንም ጠቁመው ከችግሩ ለመውጣት በትኩረት ይዞ መስራት እና አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን እንደሚገባም ተናግረው የገቢ ስራ በቅንጅት የሚሰራ በመሆኑ ተቀናጅተንና ተጋግዘን መስራት አለብንም ብለዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ጥር 28 ቀን 2018 ዓ/ም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top