ʺንጉሥ የከተመባት፣ ጀግኖች የሚወለዱባት” ደብረ ታቦር

ጀግኖች ይወለዱባታል፣ በግርማና በጀግንነት ያድጉባታል፣ የጀግንነት ታሪክም ሠርተውባታል፣ ይሠሩባታል፣ የከበሩ ታሪኮች፣ የተቀደሱ ሃይማኖታዊ ሥፍራዎች ይከቧታል፣ አበው በሰርክ ጸሎት ያደርሱባታል፣ ሊቃውንት ለደቀመዛሙርታቸው ጥበብ ይነግሩባታል፣ ደቀመዛሙርቱ ከአበው እግር ሥር ተቀምጠው ጥበብ ይቀበሉባታል፣ ምስጢር ያመሰጥሩባታል፡፡
በነጫጭ ባዝራዎች፣ በተዋቡ ድንጉላዎች የተቀመጡ ጀግኖች፣ በጦር ልብሳቸው ተውበው፣ ጦራቸውን መዘው፣ ጎራዴያቸውን ታጥቀው፣ ጋሻቸውን አስተካክለው፣ ከፊት ከኋላ በአጀብ ተከብበው፣ ሕዝብ እልል እያለላቸው ተመላልሰውባታል፣መቀመጫቸው ሆና ሀገርና ሕዝብ አሥተዳድረውባታል፡፡ ዕልፍ ታሪኮች ተሰርተውባታል፣ በሀገር ላይ የተነሱ ጠላቶች ድል ተመትተውባታል፣ እንዳይነሱ ኾነው ተቀጥተውባታል፡፡
ለሀገር ክብር፣ ለሠንደቅ ፍቅር የተነሱት ተሸልመውባታል፣ ተሹመውባታል፣ ተወድሰውባታል፣ ተሞግሰውባታል፡፡ መልካም የሠራን ማድነቅ፣ በሀገር ላይ እጁን ያነሳን ማድቀቅ ታውቅበታለች፡፡
የመንግሥት መልዕክተኞች ባሕር እየሰነጠቁ፣ የብስ እያቋረጡ፣ በበረሃና በሀሩር እየተጓዙ ከትመውባታል፣ ከኢትዮጵያውን ሹማምንት ጋር በፍቅርና በአንድነት ኖረውባታል፤ስሟን መለኮት ከተገለጠበት የታቦር ተራራ ጋር አንድ ያደረገች፣ በታቦር የተገለጠውን አምላክ በታላቅ ክብር ስታስብ የኖረች፣ እያሰበችና እያከበረች ያለች፤ የሊቃውንትና የጀግኖች ምንጭ የኾነች ጥንታዊት ከተማ ደብረ ታቦር፡፡
ኃያሉ ንጉሥ ቴዎድሮስ የድንኳኑ ማረፊያ፣ የሕልሙ መተግበሪያ ከተማ አድርጓታል፡፡ ታይቶ የማይታወቀውን ቴክኖሎጅ አስጀምሮባታል። በክብርና በሞገስ ኾኖ፣ ከፊትና ከኋላው፣ ከግራና ከቀኙ ታጅቦ፣ ታማኝ የጦር መሪዎችን እነገብርዬን እያስከተለ በጎዳናዎቿ ተመላልሶባታል፡፡
ራዕይ ቀምሮባታል፤ ሀገር የሚያጸና ትውልድ የሚያኮራ ሕልሙን ተግብሮባታል፤ ኢትዮጵያ የምትከበርበትን፣ በጠላቶቿም ዘንድ እንደተከበረችና እንደታፈረች የምትኖርበትን ስልት ቀይሶባታል፡፡ ቃሉን የማያጥፍ፣ ማተቡን የማያላላት፣ ፍርሃት ያልፈጠረበት፣ ጠላት የማይደፍረው፣ ልበ ሙሉነት የተቸረው ገብርዬ በግርማ ታይቶባታል፤ በሞገስ ኖሮባታል፤ በኃያልነት ተረማምዶባታል፡፡
በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የአለቃ ገብረሃና የባሕል ጥናት ዳይሬክተርና የታሪክ መምህሩ መሠረት ወርቁ ከተሞች አብያተ ክርስቲያናትን፣ ነገሥታትን፣ ነጋዴዎችን፣ ወታደሮችን መሠረት አድርገው ይመሠረታሉ ይላሉ፡፡
ደብረ ታቦርም ቤተክርስቲያንን መሠረት አድርጋ የተመሠረተች ናት ይሏታል፡፡ የእርሷ ምሥረታ በተነሳ ጊዜ ታላቁ ደብር ደብረ ታቦር ኢየሱስ ይነሳል፡፡
አጼ ሰይፈ አርድ በታላቁ ዙፋን ላይ ተቀምጠው ነበር፡፡ እሳቸው ከአባቶቻቸው የተቀበሏትን ሀገር ለልጆቻቸው በክብር ለማውረስ መልካሙን ኹሉ እያደረጉ ነበር፡፡ ስማቸው የሚወሳበትና የሚዘከርበት ታሪክ በምድር ጥላ ጥለው ያልፉ ዘንድ ታትረዋል፡፡ እሳቸው በነገሡም ዘመን ታሪክ የሚበዛባት፣ ወይዛዝርት እና ጎበዛዝት የሚወጡባት፣ ልበ ሙሉ ጀግኖች፣ ምስጢር አዋቂ ጥበበኞች የሚፈልቁባት ከተማ ተመሰረተች፡፡
በተራራው አናት የኢየሱስ ደብር ተደበረ፡፡ ከደብሩ መደበር ተከትላ ከተማዋ ተመሠረተች፡፡ ይህችም ከተማ አምላክ ግርማ መለኮቱን በገለጠበት የታቦር ተራራ ተጠራች፡፡ ይህች ጥንታዊት ከተማ አበው እየኖሩባት፣ ጀግኖች እየወጡባት፣ እናቶች እና አባቶች ልጆችን እየመረቁባት ዓመታትን ተሻገረች፡፡ ዘመን ዘመንን አከታትሎ ዘመነ መሳፍንት ደረሰ፡፡ በዚሕም ዘመን ደብረ ታቦር ታላቅ የፖለቲካ ማዕከል ኾነች፡፡
ደብረ ታቦር ጤናማ አየር ያላት፣ ተራራዎች የሚከቧት፣ ለጦር ሰራዊት የተመቸች፣ ለዙፋን ማስቀመጫ የተደላደለች፣ ዙሪያ ገባዋ በደን የተሸፈነች ነበረችና አስቀድመው መሳፍንቱ፣ ቆይተውም ንጉሠ ነገሥቱ ለመቀመጫቸው መረጧት፡፡
ወደዚህች ከተማ አስቀድመው በመሳፍንቱ፣ በኋላም በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የውጭ ሀገራት መልዕክተኞች መዳረሻቸው ያደርጓት፣ ይከትሙባት፣ እጅ እየነሱ ይቀመጡባት ነበር፡፡
ታላላቅ የሃይማኖት ጉባዔያት ተካሂደውባታል፤ እየመረቁባት ሀገርን የሚያጸና ምክር ንጉሡ ከመኳንንቱ፣ ከመሳፍንቱ፣ ከሊቃውንቱ፣ ከጦር አበጋዞቻቸው ጋር መክረውባታል፡፡ ደብረ ታቦር በዙሪያዋ በመንፈሳዊና በታሪካዊ ስፍራዎች የተከበበች እና የከበረች ናት፡፡ በዚህች ከተማ ውስጥ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡
እርሷ በተነሳች ቁጥር አብሮ የሚነሳው የደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን፣ የቴዎድሮስ አሻራ ያለበት የደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን እና ሌሎች አብያተክርስቲያናት የደብረ ታቦርን ታሪካዊነት የሚመሰክሩ፣ የኢትዮጵያን እውነትና ታሪክ የሚዘክሩ ናቸው፡፡
የደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ዳዊት እየደገሙ ያደጉበት ነው፡፡ እቴጌ ጣይቱ የተለወዱ በዚህችው ታሪካዊት ከተማ ነው፡፡ በተክሌ አቋቋም ፣ ቁጥራቸው የበዛ ደቀመዛሙርት የሚወጡበት ታላቅ ስፍራ የሚገኘውም በዚህችው ከተማ ነው፡፡
ሴባስቶፖል የተሠራባት፣ የቴዎድሮስ ራዕይ የተሞከረባት፣ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀ ሠራዊት የመገንባት ሕልም የተጀመረባት ጋፋትም የደብረ ታቦርን ስልጣኔ፣ ታሪክ የምትመሰክር በዚሕችው ጥንታዊት ከተማ በአቅራቢያ የምትገኝ ናት፡፡
ደብረ ታቦር የአጼ ቴዎድሮስ ሠርግ የተሰረገባት፣ ታላቅ አጀብ የበዛላት፣ ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ የተወለደባት ታላቅ ደስታ የታየባት፣ ታላቅ ጥበብ የተሞከረባት ከተማ ናትም ብለውኛል መምህሩ፡፡ ይህች ከተማ የዕደ- ጥበበኞች፣ የብልሆች፣ የባለ ታሪኮች፣ የባለ ራዕዮች ከተማም ናት፡፡
ደብረ ታቦር የጥንቱን፣ የመካከለኛውን፣ የዘመናዊውን እና የአኹኑን የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያውቁባት፣ የኢትዮጵያን ታላቅነት እና ቀደምትነት የሚመሰክሩባት ከተማም እንደኾነች ነግረውኛል፡፡ ኢትዮጵያን ከጥንት እስከ ዛሬ ማየት የፈለገ ኹሉ ደብረ ታቦር ይገኝም ነው ያሉኝ፡፡
ጀግኖች የሚመላለሱበት ዓለም ሳጋ፣ ምንጮች የሚፈልቁበት ጉና ተራራም በዚህችው ከተማ አቅራቢያ የሚገኙ ድንቅ የተፈጥሮ ስጦታዎች ናቸው፡፡
የደብረ ታቦር ዪኒቨርሲቲ የአካባቢው ታሪኮች እንዲታወቁ፣ እንዲጠበቁ፣ ጎብኚዎች እንዲደርሱባቸው እና አውቀው እንዲያሳውቋቸው እያደረገ መኾኑን ነግረውኛል፡፡
በተለይም በዓለ ቅዱስ መርቆሪዮስ እና በዓለ ደብረ ታቦር በታላቅ ክብር እንዲከበሩ እያደረገ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ዓላማ የተደበቁ ታሪኮች እንዲወጡ፣ ሕዝቡም ሃብቴ ነው ብሎ እንዲጠብቃቸው ማድረግ ነው ብለውኛል፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ታላላቅ የሃይማኖት ጉባዔ እንዳደረጉባት ኹሉ በዚህ ዘመንም የታላላቅ ጉባኤ መከወኛ ከተማ መኾን አለባትም ይላሉ፡፡
በወረሃ ጥር ደብረ ታቦር ትሸለማለች፣ ሊቃውንቱን ከየአድባራቱና ከየገዳማቱ ታሳባስባለች፣ ምዕምናን ነጫጭ እየለበሱ ጎዳናዎቿን ይሞሏታል፣ ጎበዛዝቱ ትጥቃቸውን እያሳመሩ፣ ጎፈሬያቸውን እያስተካከሉ፣ ቤልጅግና ምንሽራቸውን፣ አብራራውና ክላሻቸውን እያዩ በኩራት ይታዩባታል፤ ወይዛዝርቱ በሀገርኛ ልብስ ተውበው፣ ሹርባቸውን ተሰርተው፣ ባሕልና ወጉን ጠብቀው ሲወጡ ይታያሉ፡፡
ባሕልን፣ ታሪክን፣ ሃይማኖትን፣ እሴትን፣ አንድነትን፣ ኢትዮጵያዊነትን እና ጀግንነት ያዩ ዘንድ ወደ ጥንታዊቷ ከተማ ይጓዙ፡፡ ትናንትን ከዛሬ፣ የዛሬውን ከነገ ጋር እያስተሳሰረች፣ እየገመደችና እያስማማች ታሳየለች:- ደብረ ታቦር፡፡
#በታርቆ ክንዴ
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ጥር 17 ቀን 2018 ዓም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top