የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር “የኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት ንቅናቄን” በሚፈለገው መንገድ ለማስኬድ እና የቅዱስ መርቆሪዮስ ክብረ በዓል በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር እንዲሁም የፈረስ ጉግሱ ባደገ ደረጃ እንዲካሄድ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ እና ከደብረታቦር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱ ላይ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሀላፊ አቶ አስራት መሰለ እንደገለጹት በከተመዋ ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፉ በርካታ ምቹ ሁኔታ ያለ መሆኑን ጠቅሰው “የኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት ንቅናቄን” በጥሩ መንገድ ለማስኬድ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አንስተው ንቅናቄውን በአግባቡ ማስኬድ ከተቻለ የተቀዛቀዘውን ዘርፍ ለማነቃቃት እና የተሻለ እንቅስቃሴ ለመፍጠር መልካም አጋጣሚ በመሆኑ ንቅናቄውን የተሳካ ለማድረግ ሁላችንም በባለቤትነት ይዘን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ እና ከደብረታቦር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በጋራ መስራት የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማዘመን፣ በተቋሙ ያለውን የሰው ሀይሉ በእውቀትና በክህሎት ለማብቃት እና የቴክኖሎጅ ሽግግር ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልፀው ይህም ዘርፉን በተሻለ መንገድ ለማስኬድ እና ውጤታማ ለማድረግ ላቅ ያለ ፋይዳ መኖሩን ጠቁመው የከተመዋን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፍ በሚፈለገው አግባብ ለማስኬድ በቅንጅት መስራት አለብንም ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ሀብቴ አለማየሁ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ በሚቻለው ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ እና በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልፀው ዘርፉን በላቀ ደረጃ ለማስኬድ ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
በባለፉት አመታት ለቅዱስ መርቆሪዮስ ክብረ በዓል እና ለፈረስ ጉግሱ በተለያየ መንገድ እገዛ ሲደረግ እንደነበርም አውስተው ለዚህ አመት የቅዱስ መርቆሪዮስ ክብረ በዓል እና የፈረስ ጉግስም እገዛ እንደሚደረግ ገልፀው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ስራዎችን ተቀራርቦና ተረዳድቶ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ አካላትም በሰጡት ሀሳብ ደብረታቦር እና አካባቢው ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ትልቅ ፀጋ ያለው በመሆኑ ዘርፉን በሚፈለገው መንገድ ለማስኬድ በቅንጅትና በትብብር መስራት እንደሚገባ አንስተው የተቀዛቀዘውን ዘርፍ ለማነቃቃትና ወደ ጥሩ ደረጃ ለመውሰድ ሁላችንም በትኩረት ይዘን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
በከተመዋ በየአመቱ የሚከበረው የቅዱስ መርቆሪዮስ ክብረ በዓል እና የሚካሄደው የፈረስ ጉግስ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑንም ጠቅሰው የዚህ አመት ክብረ በዓል ከእስካሁኑ በበለጠ ሁኔታ እንዲከበር እና የፈረስ ጉግሱም በላቀ መንገድ እንዲካሄድ ሁሉም በባለቤትነት መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን እንዳሉት የሰላም እጦቱ በከተመዋ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሮ መቆየቱን ገልፀው በአሁኑ ጊዜ የተሻለ ሰላም በመኖሩ ከተመዋን ለማልማት እና የተቀዛቀዘውን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማነቃቃት ሁላችንም በባለቤትነት ይዘን ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
በተለያየ አካባቢ የሚኖሩ ወገኖቻን በከተመዋ ተገኝተው የቅዱስ መርቆሪዮስን ክብረ በዓል እንዲያከብሩ እና የፈረስ ጉግሱንም እንዲታደሙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ክብረ በዓሉ እና የፈረስ ጉግሱ የከተማችን ገጽታ ለመገንባት እና የቱሪዝሙን እንቅስቃሴ ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ባማረና በደመቀ መንገድ እንዲካሄድ ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብንም ብለዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ጥር 12 ቀን 2018 ዓ/ም
