ደብረታቦር ከተማ በ14ኛው ክፍለ ዘመን በ1327 ዓ/ም በአጼ ሰይፈ አርዕድ የተመሰረተች ስትሆን ለበርካታ አመታት የማዕከላዊ መንግስት መቀመጫ በመሆን አገልግላለች። ተስማሚ የአየር ንብረትን ከጣና እና ከጉና አዋህዳ የምትመግብ ሲሆን የአየር ንብረት ተስማሚነቷና ተፈጥሯዊ አቀማመጧ ለረጅም አመታት የማዕከላዊ መንግስት መቀመጫ እንድትሆን ተመራጭ አድርጓታል።

በዘመነ መሳፍንት ወቅት ለመሳፍንቶች ተመራጭ ከተማ እንደነበረች የታሪክ ድርሳናት የሚያስረዱ ሲሆን ከዘመነ መሳፍንት መክሰም በኋላም ታላቁ ንጉስ አጼ ቴዎድሮስ በዋና ከተማነት መርጠው መዲናቸው አድርገው ተጠቅመውባታል። ደብረታቦር የብዙ ነገስታቶች መዲና የነበረች ከተማ መሆኗን አሁንም ድረስ የሚገኙት የቤተመንግስታት ፍርስራሾች ምስክር ናቸው፡፡
ቱባ ባህል፣ ሰፊ ታሪክ፣ ውብ ተፈጥሮ ያደላት ደብረታቦር ታህሳስ 29 የገና በዓልን በታላቁ ደብር ርእሰ አድባራት ደብረታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን በድምቀት በማክበር በከተመዋ የሚከበሩትን በርካታ በዓላት ማክበር ጀምራለች፡፡ በተንጣለለው አጅባር ሜዳ ላይ ጥር 11 የጥምቀት በዓል በደማቅ ሁኔታ የሚከበር ሲሆን እስከ ጥር 29 በየእለቱ በሚባል ደረጃ በርካታ ሐይማኖታዊ በዓላት የሚከበሩባት ብቸኘዋ ከተማ ናት፡፡
በቀድሞ ዘመን የውጭ ሀገራት በሚፈጥሩት ተጽዕኖ በተለይም ከጣሊያን ጋር የነበረውን የህዝብ ተጋድሎ የሚዘክረውና ዘመናትን ያስቆጠረው በቡድን ተከፋፍለው በልምጭ /ስሚዛ/ እንጨቶች የሚከናወነው የፈረስ ጉግስ ፍልሚያም የከተማዋ የቆዬ መገለጫ ባህል ነው።
በደብረታቦር አጅባር ሜዳ ላይ በየዓመቱ ጥር 25 የሰመዓቱ ቅዱስ መርቆሪዮስ ንግስ በዓል በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ የመጣ ሲሆን የበዓሉን አከባበር ምክንያት በማድረግ የሚካሄደው የፈረስ ጉግስም በሚያምርና በሚስብ መልኩ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በከተመዋ የዘንድሮውን ዓመት የቅድስ መርቆሪዮስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ከእስካሁኑ በበለጠ መንገድ ለማክበር እና የፈረስ ጉግሱንም በላቀ ደረጃ ለማስኬድ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡
ክብረ በዓሉን እና የፈረስ ጉግሱን የከተመዋና አካባቢው መገለጫ ለማድረግ እና በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ከፍ ባለ ደረጃ እንዲካሄድ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በባለቤትነት ይዞ ሊሰራ ይገባል፡፡
ደብረታቦር እና አካባቢው በርካታ የመስህብ ሀብቶች ያሉት ሲሆን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የምትኖሩ ወገኖች በከተመዋ በመገኘት የሰማእቱን ቅዱስ መርቆሪዮስ ክብረ በዓልን እንድታከብሩ እና የፈረስ ጉግሱን እንድትታደሙ እንዲሁም ያሉትን የመስህብ ሀብቶች እንድትጎበኙ መልእክታችን እናስተላልፈለን፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ጥር 06 ቀን 2018 ዓ/ም
