ስነህዝብ በተገቢው ሁኔታ ከተሰራበት ለሀገር እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ተግባሩን በሚፈለገው መንገድ ለማስኬድ ሁሉም አካል በትኩረት ይዞ ሊሰራ እንደሚገባ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ፕላንና ልማት ቡድን አስገንዝቧል፡፡
በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት የፕላንና ልማት ቡድን መሪ ቄስ አወቀ አለማየሁ እንደገለጹት አንድን ሀገር ሀገር ሊያሰኘው የሚያስችለው መሰረቱ ህዝብ እንደ መሆኑ መጠን የሀገር እድገት መሰረታዊ መለኪያውም የህዝቡ ልማት ወይም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት መሆኑን ተናግረው ስነህዝብ የአንድን ህዝብ የተለያዩ ገጽታዎችን በመተንተን የሚያሳይ ሳይንስ መሆኑን እና የአንድ አካባቢ ስነህዝብ ሁኔታ በህዝብ ብዛት፣ በፆታና ዕድሜ ቅንብር፣ በህዝብ እድገት ምጣኔ እና በህዝብ አሰፋፈር የሚተነተን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ስነህዝብና ልማት የማይነጣጠሉ ጉዳዮች መሆናቸውንም ጠቁመው ስነህዝብ ለማህበረሰቡና ለሀገር ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው መሆኑን አንስተው በዚህም የልማት ስራዎችን ለመስራት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራትን በአግባቡ ለማከናዎን ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልፀው ስነህዝብን በሚፈለገው መንገድ ለማስኬድ ሁሉም አካል በትኩረት ይዞ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የስነህዝብ ጉዳዮችን በልማት እቅድ ሂደት የማካተት አስፈላጊነት የሚመነጨው ስነህዝብና የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አንዱ ከሌላው ጋር ካላቸው የማይነጣጠል ትስስር መሆኑንም ተናግረው ህዝብ የልማት ዓላማ ወሳኝ ግብአት ስለሆነ፣ ህዝብ የልማት አምጭም ተጠቃሚም በመሆኑ እንዲሁም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲሞግራፊያዊ፣ አካባቢያዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች እርስ በእርሳቸው የተዛመዱና በልማት ሂደቶች ላይ ከቤተሰብ እስከ ሀገራዊ ደረጃ ተጽእኖ የሚያሳድሩ በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡
ቡድን መሪው አያይዘውም ስነህዝብ ለአንድ ሀገር እድገትም ሆነ ውድቀት አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን አንስተው ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራበት ለሀገር እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በአንጻሩ በትኩረት ተይዞ ካልተሰራበት ደግሞ ውድቀትን የሚያስከትል መሆኑን ጠቁመው እንደ ከተማ አስተዳደር የስነህዝብ ተግባርን በጥሩ መንገድ ለማስኬድ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ከስነህዝብ ጋር ተያይዞ የመንግስት አካሉን እና የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በተለያየ አግባብ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ፣ በትምህርት ቤቶች ክበባት እንዲቋቋሙ እየተደረገ መሆኑን እና ሌሎችም ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው ስነህዝብን በሚፈለገው አግባብ ለመተግበር ሁላችንም በባለቤትነት ይዘን ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የስነህዝብ መልካም አጋጣሚ አምራች ሀይል የሆነው ወጣቱ ክፍል በብዛት ሲኖር የሚፈጠር መሆኑን እና ይህም ለሀገራችን እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልፀው ስነህዝብ ለማህበረሰቡና ለሀገር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ተግባሩን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስኬድ ሁሉም አካል ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ፕላንና ልማት ቡድን መሪ ቄስ አወቀ አለማየሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ታህሳስ 15 ቀን 2018 ዓ/ም
