“የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ቱርፋቶች” በሚል መሪ ሀሳብ የአማራ ክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በወቅታዊ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ከደብረታቦር ከተማ አስተዳደር እና ከደቡብ ጎንደር ዞን ህዝብ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን እንዳሉት እንደ ሀገር በርካታ የልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን እና በደብረታቦር ከተማም የተለያዩ የልማት ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን አንስተው የሰላም እጦቱ በብዙ መንገድ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን ጠቁመው ሰላምን ለማምጣት ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በትኩረት ይዞ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ታጣቂ ሀይሉ በርካታ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም ጠቅሰው ሰላምን በማረጋገጥ ከገባንበት ችግር ለመውጣት እና የእለት ከእለት እንቅስቃሴያችን ለማስኬድ እንዲሁም የልማትና ሌሎችንም ስራዎች በአግባቡ ለመስራት ሁላችንም በባለቤትነት ይዘን ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ ዶክተር ዘርይሁን ፍቅሩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ከለውጡ ወዲህ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀው የውስጥና የውጭ ጠላቶች በጋራ ሁነው እየፈፀሙት ባለው እኩይ ድርጊት የተለያየ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን እና ላለንበት የሰላም እጦት ምክንያት መሆኑን አንስተው መንግስት እየሰራቸው ባሉት ስራዎች ሰላሙ ላይ መሻሻል መምጣቱን ጠቁመው አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ለማድረግ ሁላችንም መስራት አለብን ብለዋል፡፡
ታጣቂ ሀይሉ በአማራ ህዝብ ጥያቄ ሽፋን የተለያዩ ጥፋቶችን እያደረሰ መሆኑንም ጠቅሰው የዚህን ሀይል እኩይ ድርጊት ማውገዝና ይበቃል ማለት እንደሚገባ አስገንዝበው መንግስት ሁሌም ለሰላም በሩ ክፍት በመሆኑ ችግሮችን በውይይትና በምክክር ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረው አሁንም የታጠቁ ሀይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎችም በሰላም፣ በልማት፣ በመልካም አስተዳደር እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ቢደረጉ ያሏቸውን ሀሳቦች አንስተዋል፡፡ በችግር ውስጥ ተሁኖም መንግስት በርካታ ስራዎች መስራቱን ተናግረው ባለው ግጭትና ጦርነት ሰፊ ጉዳት እየደረሰ በመሆኑ ሰላም እንዲመጣ ለማድረግ ሁላችንም ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡ የህዝቡን ጥያቄዎች የሚመልሱ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግም ጠቁመው በከተመዋ ለመስራት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው ፕሮጀክቶች እንዲሰሩ እና ተጀምረው ብዙ አመት የሆናቸው ደግሞ እንዲጠናቀቁ ጠይቀዋል፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ደጀኔ እንደተናገሩት ስለ እውነት በመቆም ትክክለኛውን መንገድ ይዞ መጓዝ እንደሚያስፈልግ አንስተው ግፍ እየፈፀሙ ካሉ ሀይሎች ጋር መሆን እንደማይገባ እና ድርጊታቸውንም ማውገዝ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው የፀጥታ ሀይሉ ተቀናጅቶ በመስራቱ ወንጀለኞች ወደ ህግ እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑም ጠቁመው ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ በመሆኑ ሰላምን ለማምጣት ሁላችንም መስራት አለብን ብለዋል፡፡
የአብክመ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ በርይሁን መንግስቱ እንደገለጹት ክልላችን እና ሀገራችን በግጭና በጦርነት እንዲኖሩ የሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ጠላቶች እየሰሩት ባለው ሴራ የሰላም እጦት መፈጠሩን እና የፀጥታ ሀይሉ በሰራው ስራ መሻሻል መምጣቱን አንስተው ሰላምን በማረጋገጥ ከገባንበት ችግር ለመውጣት ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበው በችግር ውስጥ ተሁኖም በርካታ መልካም ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ ዶክተር ዘርይሁን ፍቅሩ የውይይት መድረኩን አጠቃለዋል፡፡ በህዝብ ላይ በደል እያደረሱ ያሉትን የጥፋት ሀይሎች ማህበረሰቡ በድፍረት መታገል እንዳለበት አስገንዝበው የስራ ሀላፊዎችና መንግስት ሰራተኞች ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ልትሰጡ ይገባልም ብለዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ታህሳስ 16 ቀን 2018 ዓ/ም
