መሬት ውድ ሀብት በመሆኑ ካለ አግባብ እንዳይባክን መመሪያን ተከትሎ መስራት እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ፡፡

የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር መሬት መምሪያ በስራ ላይ ያለውን የገጠር መሬት አስተዳደር መመሪያ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ በመምሪያው የገጠር መሬት አስተዳደር ቡድን መሪ / በላይነሽ ገደፋው በስራ ላይ ያለውን የገጠር መሬት መመሪያ አስመልክተው ሰነድ አቅርበዋል፡፡ በቀጣይ ከሚካሄደው የቦታ ምሪት ጋር ተይዞ ባለይዞታዎችን እንዲሁም እድሜያቸው የደረሱትን ልጆችና የሚመለከታቸውን ወገኖች ለማስተናገድ በተመረጡት ኮሚቴዎች አማካኝነት የምዝገባና ምልመላ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተው በቅርቡ ደግሞ የትችት ስራው እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

በስራ ላይ ያለው መመሪያ በሚፈቅደው መሰረት ስራዎችን መስራት እና ዜጎችን ማስተናገድ እንደሚገባም አንስተው ከመመሪያ ውጭ የሚሰራ ስራ ተጠያቂነትን የሚያስከትል በመሆኑ መመሪያውን ተከትሎ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው ሁላችንም ስራውን በባለቤትነት ይዘን መስራት አለብን ብለዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላትም በሰጡት ሀሳብ በስራ ላይ ያለውን የገጠር መሬት አስተዳደር መመሪያ ተከትለው ስራቸውን እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀው የሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና የማይመለከታቸው ደግሞ እንዳያገኙ ለማድረግ በትኩረት ይዘን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

በስራ ላይ ያለው መመሪያ ያልመለሳቸው ጉዳዮች መኖራቸውን እና ግልፀኝነት እንደሚጎድለው ጠቁመው ቢስተካከሉ ያሏቸውን ነገሮች አስመልክተው ሀሳቦችን አንስተው አርሶ አደሩን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ስራው መሰራት እንዳለበት ተናግረው ህገወጥነት እና ካለአግባብ አካሄድ እንዳይኖር ሁላችንም ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን ብለዋል፡፡ 

የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር መሬት መምሪያ ሀላፊ አቶ ንጉሴ አሉበል እንደገለጹት በስራ ላይ ያለው የገጠር መሬት አስተዳደር መመሪያ በሚፈቅደው መንገድ ዜጎችን ማስተናገድ እንደሚያስፈልግ አንስተው መመሪያውን በደንብ ተረድቶ ስራን መስራት እንደሚገባ እና የማይመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳይካተቱ ኮሚቴው በጥንቃቄ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የቤተሰብ ምዝገባ ምልመላና ትችት ስራውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት ይዞ መስራት እንደሚገባም ተናግረው የሚቀርቡ ማስረጃዎችን በአግባቡ መለየት እና በተለያየ መንገድ የማጥራት ስራን መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው ማህበረሰቡን በፍትሀዊነት ተጠቃሚ ለማድረግ መስራት አለብንም ብለዋል፡፡

የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀይለኢየሱስ ሰለሞን እንደተናገሩት መሬት መምሪያው ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ ከሚኖረው የቦታ ምሪት ጋር ተያይዞ እየተሰሩ ያሉት ስራዎች የመዘግየት ሁኔታ የሚታይባቸው በመሆኑ ማፍጠን እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ያለውን የገጠር መሬት አስተዳደር መመሪያ መሰረት አድርጎ ስራዎችን መስራት እንደሚገባም ጠቁመው ከመመሪያው ውጭ አንድም ነገር መስራት ተገቢ አለመሆኑን አስገንዝበው ኮሚቴው ተቆራርጦ መመሪያውን ባከበረ መንገድ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበው አርሶ አደሩን ተጠቃሚ በሚያደርግ እና ተመሪውንም በማይጎዳ አግባብ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

 

  ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ታህሳስ 20 ቀን 2018 /

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top