“ከስትራቴጅክ ኩስምና ወደ ላቀ ቁመና” በሚል መሪ ሀሳብ በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ እና በሶስቱ ክፍለ ከተሞች ላሉ የፖሊስ አመራርና አባላት በተቋማዊ ሪፎርም አተገባበር እና በጅኦስትራቴጅካዊ የፖሊስ አመራር ዙሪያ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን እንዳሉት የመንግስት ዋና ተግባር ህግ ማስከበር እና የህዝቡን ደህንነት መጠበቅ መሆኑን አንስተው ህግን በአግባቡ ለማስከበር እና የህዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ ደግሞ የፖሊስ ተቋሙ ጠንካራ መሆን እንዳለበት ገልፀው ለዚህሞ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በቀደሙት አመታት የፖሊስ ተቋሙ ከአደረጃጀት ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንደነበሩበት አስታውሰው ከቅርብ አመታት ወዲህ ተቋሙ ላይ ለውጥ ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ በመሆኑ ለውጦች እየመጡ መሆናቸውን ገልፀው አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡
ከንቲባው አክለውም የፖሊስ ተቋሙ ክብር የሚወሰነው በተቋሙ አመራርና አባል ስነምግባር እና የተግባር አፈጻፀም መሆኑን ጠቁመው የፖሊስ አመራሩና አባሉ በሚያደርገው ያልተገባ ድርጊት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለፖሊስ ያለው አተያይ እና ክብር እየቀነሰ የመጣበት ሁኔታ እንደነበር አውስተው የለውጥ ስራው ፖሊስን ወደ ከፍታው ለመመለስ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረው ስልጠናውን በአግባቡ በመውሰድ በስነምግባር መታነጽ እና ተግባራትን በተገቢው ሁኔታ መፈፀም እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በሚቆየው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናው በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ለፖሊስ አመራሩና አባሉ ስልጠና እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን እና የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ሀላፊ ኮማንደር ያለው ዘለቀ ተገኝተዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ታህሳስ 23 ቀን 2018 ዓ.ም
