በመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሀሳብ ለደቡብ ጎንደር ዞን ወረዳዎች እና ለደብረታቦር ከተማ አስተዳደር የክፍለ ከተማና የቀበሌ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ማጠቃለያ መድረክ ተካሂዷል፡፡


በማጠቃለያው መድረክ ላይ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ደጀኔ እንደተናገሩት የአመራሩን አቅም በማሳደግ ተግባራትን በጥሩ መንገድ እንዲፈጽም ለማድረግ ስልጠናው ሲሰጥ መቆየቱን አንስተው አመራሩ የሰላምን አስፈላጊነት ተረድቶ ሰላም እንዲመጣ መስራት እንዳለበት አስገንዝበው አሁን ያለውን የተሻ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገርና ሰላምን ለማጽናት ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የመልካም አስተዳደር ችግር ለተፈጠረው የሰላም እጦትና አለመረጋጋት መንስኤ በመሆኑ ህዝቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍታት የአመራሩ ቀዳሚ ተልእኮ መሆኑን ገልፀው ፈጣንና ቀልጣፋ ውሳኔ መስጠት፣ የግልፀኝነትንና የተጠያቂነትን አሰራር ማስፈን እንደሚገባም አስገንዝበው የማህበረሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ እና የመፈፀም አቅምን ማጎልበት አለብን ብለዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው አያይዘውም የግብርና፣ የትምህርት፣ የገቢ፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ የቱሪዝም፣ የከተማና መሰረተ ልማት ስራዎችን እና ሌሎችንም ተግባራት በአግባቡ ማከናዎን እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው ስራዎችን በጊዜ የለኝም መንፈስ መስራት እንደሚገባ አንስተው በጫካ ያሉ ታጣቂ ሀይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ ለማድረግ እንዲሁም አንድነትንና አብሮነትን ለማጠናከር መስራት አለብን ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን በበኩላቸው ተግባራትን በአግባቡ ለመፈፀም አመራሩ በትኩረት ይዞ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመው የገቢ ስራን ከወዲሁ ለማጠናቀቅ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረው ሁላችንም በባለቤትነት ይዘን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
ስራዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመስራት የአስተሳሰብና የመተግበር ትስስር ሊኖር እንደሚገባም አስገንዝበው ተግባራትን በሚፈለገው አግባብ በመፈፀም ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ይዞ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረው ስራዎችን በቅንጅትና በትብብር ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
በስልጠናው ሲሳተፉ ከቆዩት አመራሮች መካከል ሀሳባቸውን የሰጡ አመራሮች እንዳሉት ከስልጠናው ጥሩ እውቀት ማግኘታቸውን እና ያገኙትን እውቀት በአግባቡ ተጠቅመው ስራዎችን በተሻለ መንገድ እንደሚሰሩ ገልፀው እያጋጠመን ካለው ችግር ለመውጣት ተቀናጅተንና ተናበን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
የሰላም እጦቱና አለመረጋጋቱ ዘርፈ ብዙ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ ሰላም እንዲመጣ ለማድረግ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም ተናግረው ህብረተሰቡም ማገዝና መተባበር እንዳለበት ጠቁመው የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ እንሰራለን ብለዋል፡፡
በስልጠናው ማጠቃለያ መድረክ ላይ የደቡብ ጎንደር ዞን እና የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር አስተባባሪዎች ተገኝተዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ታህሳስ 02 ቀን 2018 ዓ/ም
