ሱስና ሱሰኝነት እያደረሰ ያለው ተጽእኖ!!

ሱስ ማለት ሱስ አምጭ የተባለው ነገር ተደጋግሞ እንዲወስድ የሚገፋፋ መጥፎ ልምድ ወይም ሁኔታ ማለት ነው፡፡ ሱስ እንደሚወሰደው ነገር፣ አይነት እና አንደ አወሳሰዱ ሁኔታ እንዲሁም አንደ ወሳጁ የአእምሮና የአካል አቋም የሱስ አይነት ወይም ደረጃ ሊለያይ ይችላል፡፡
በሱስ ለመያዝ ዋና መነሻ ተብሎ የሚታመነው ሱስ አምጭው ነገር ከተወሰደ በኋላ በቅድሚያ የሚፈጥረው “ደስታ” የእርካታና የድል ስሜት ነው፡፡ ይህ የአእምሮ ሁኔታ ሱስ አምጭውን ነገር በማከታተል እንዲወስድ ይገፋፋል፡፡ ከዚህ ተጨማሪም የሚወስደው ነገር መጠን እንዲጨምር ያደርጋል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ሲታይ አብዛኛው ሰው ሱስ እየሆነበት የሚገኘው የአልኮል መጠጥ፣ ሲጋራ፣ ጫት፣ ሀሽሽ እና ሲሻ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከነዚህም መካከል አንደ አገርም ሆነ እንደ አካባቢያችን የአልኮል መጠጥ፣ ሲጋራ እና ጫት ለአብዛኛው ወጣት የእድገት ማነቆ ሆኗል፡፡
በተለይም በዪኒቨርሲቲዎች ያለ ጫት ምንም ነገር መስራት አይቻልም እስከ ማለት የደረሱ ተማሪዎች እየተበራከቱ ነው፡፡ ይሁን እንጅ እንደ ዚህ የሚሉ ተናጋሪዎች ያለ ጫት ብዙ ዜጎች ታሪክ መስራታቸውን ዘንግተውት ሳይሆን ለሱሰኝነታቸው መጠለያ ያገኙ መስሏቸው መሆኑን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ይመሰክራል፡፡
ትንባሆ፡- ትንባሆ በኢትዮጵያ ውስጥ በሲጋራ መልኩ እየተጨሰ የሚወሰድ ሲሆን ጊዜያዊ ስሜትን ያነቃቃል፡፡ ይሁን እንጅ የደም መብዛት፣ የልብ ህመም፣ የሳንባ በሽታ፣ የተለያዩ የካንሰር በሽታዎችን እና የጥርስ መበላሸትን የሚያስከትል ነው፡፡
ጫት፡- ጫት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተመረተ ለኛው ለኢትዮጵያዊያን የእድገት ማነቆ የሆነ ቅጠሉ እየተቀነጠሰ የሚበላ ወይም የሚቃም ነው፡፡ ጫት ለሻጩ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ቢሆንም ለገዡ ወይም ለተጠቃሚው ከገቢም ሆነ ከስዕብና አንጻር ከፍተኛ ውድቀት የሚያስከትል ነው፡፡
በመሆኑም ለረጅም ጊዜ ከተወሰደ በቀላሉ ተናዳጅነትን፣ መሸበርን፣ መንቀዥቀዥን፣ መደበርን፣ በፍጥነት ተለዋዋጭነትን የሚያመጣ ሲሆን የደም መብዛትን፣ የሆድ ድርቀትን፣ የጉበት መጎዳትን፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስን እና የጥርስ መበላሸትን ያስከትላል፡፡
የአልኮል መጠጥ፡- ይህ ሱስ አምጭ ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ወይም በመጠኑ ሲወሰድ የማነቃቃት ሀይል ያለው ሲሆን መጠጣቱ ሲቀጥል ግን ከማነቃቃቱ አልፎ የማደንዘዝ ወይም ራስን የመቆጣጠር ችሎታን የሚያሳጣ ይሆናል፡፡ ረዘም ላለ ጊዜ ሲወሰድ የጉበትና የልብ በሽታን፣ የደም መብዛትን፣ የአእምሮ እና የነርብ ህመምን እንዲሁም ሌሎች ችግሮችን ያስከትላል፡፡
እነዚህ ሱሶች ከግለሰብ አልፎ በአገርም የስነ-ምግባር አጥሮችን በመጣስ ግብረ-ገብነትን እና ህሌና-ቢስነትን አስፋፍተዋል፤ ሱሰኛው ሱሱን ለማርካት ገቢ የሚያስፈልገው በመሆኑ ያን ገቢ ደግሞ በራሱ ማግኘት ካልቻለ ወደ ሌላ ወንጀል ተሰማርቶ ሱሱን ለማርካት መንቀሳቀሱ አይቀሬ ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ ከስርቆት፣ ከዘረፋ ብሎም ከሙስና ወንጀል ውስጥ መዘፈቁ ግድ ይሆንበታል፡፡ ሙሰኝነቱ ደግሞ እንዲሁ ገደብ ያለው ሳይሆን የወገንን እና የአገርን ጥቅም አሳልፎ እስከ መስጠት ያደርሳል፡፡
ሱሰኞች በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ወደ ሱስ ይገባሉ፤ ይሁን እንጅ ለመግባት የቀለላቸውን ያህል ግን ለመውጣት ይቸገራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የሚገባው እንጅ የሚወጣው ሰው አነስተኛ በመሆኑ ሱሰኞቹ በመበራከት ላይ ይገኛሉ፡፡
በመሆኑም ይህ ብዙ ተስፋ የሚጣልበት ትውልድ ችግሮችን ለመርሳት ለሱስ ከሚዳርጉ ነገሮች ውስጥ ከመግባት ይልቅ ችግሮቹን ተጋፍጦ ሊያሸንፍ ይገባል፤ በሱስ ተይዞ ጊዜውን በጫት እና በሺሻ ቤቶች ከማሳለፍ ይልቅ አፍላ ጉልበቱን ተጠቅሞ በመስራት ራሱን፣ ቤተሰቡን ብሎም አገርን ሊለውጥ ይገባል፡፡
ስለሆነም ከአቅም በላይ እየጠጡ ጊዜንና ገንዘብን ከመጨፍጨፍ እንዲሁም በስካር መንፈስ ከቤተሰብ ብሎም ከጎረቤት እና ከጓደኛ ጋር በመጋጨት ከክብር ይልቅ ንቀትን ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን ከማትረፍ ራሱን ከሱስ የፀዳ አድርጎ የቤተሰብን ክብር አስጠብቆ በአካባቢም ክብርን እና ፍቅርን ተችሮ መኖር አቻ የሌለው የህይዎት መንገድ ነው፡፡
በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸውን በተገቢው ሁኔታ ቁጥጥርና ክትትል አድርገው በስነምግባር ማሳደግ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ህብረተሰቡ፣ መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ሱሰኝነትን ማውገዝና መምከር አለባቸው፡፡
ትውልዱም ከሱሰኝነት ነጻ በመሆን የራሱን ጤና ከመጠበቅ እና ገንዘቡን ካለአግባብ ከማባከን ወጥቶ የማህበረሰቡ አለኝታ እና የአገር ዋልታና ማገር ሊሆን ይገባል እንላለን፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ህዳር 26 ቀን 2018 ዓ/ም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top