ከማህበረሰቡ እሴት በመውጣት እየተፈፀመ ያለውን ጾታዊ ጥቃት ለማስቆም ሁሉም አካል በባለቤትነት ይዞ መስራት እንዳለበት ተገለፀ፡፡

የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ በአለም ለ34ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ20ኛ ጊዜ “ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበረውን የፀረ ጾታዊ ጥቃት ቀንን አስመልክቶ ከባለድርሻና አጋር አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት የወንጀል ጉዳይ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ፍስሀ አስማረ ከአለም አቀፉ የፀረ ጾታዊ ጥቃት ቀን ጋር አያይዘው ሰነድ አቅርበዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እየጨመሩ መሆናቸውን ገልፀው አካላዊ፣ ወሲባዊና ስነልቦናዊ ጥቃቶች በአብዛኛው ሴቶችና ህጻናት ላይ እየተፈፀሙ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ጾታዊ ጥቃት የጤና እክል፣ የኢኮኖሚ ጥገኝነት፣ ስነልቦናዊና ማህበራዊ ችግሮች፣ የሰባዊ መብት ጥሰቶችና ሌሎችንም ተያያዥ ጉዳቶች እያደረሰ መሆኑን ጠቅሰው ድርጊቱን ለማስቆም ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በትኩረት ይዞ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበው ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር፣ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከርና ተጎጅ ወገኖችን መንከባከብ አለብንም ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላትም በሰጡት ሀሳብ ጾታዊ ጥቃት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ በመኖሩ ድርጊቱን ለማስቆም በትብብር መስራት እንደሚገባ ተናግረው ወንጀሉን በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ አስተማሪ ህጋዊ እርምጃ መወሰድ አለበት ብለዋል፡፡ በሰላም አለመኖሩ የተነሳ በተለያየ አግባብ ሴቶችና ህጻናት ላይ ጾታዊ ጥቃት እየተፈፀመ መሆኑንም ጠቁመው ከሰውነት እየወጣን ያለንበት እና በሌሎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እያዩ እንዳላዩ የማለፍ ሁኔታ ያለ በመሆኑ መስተካከል እንዳለበት አንስተው ድርጊቱን ለማስቆም መንግስትና ህብረተሰቡ በትኩረት ይዘው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ተወካይ ሀላፊ አቶ ተስፋ ግዛቴ እንደገለጹት ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣበት አግባብ መኖሩን እና ድርጊቱ ዘርፈ ብዙ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አንስተው እየተፈፀመ ያለውን ጾታዊ ጥቃት ለማስቆም በቅንጅት ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
ከአለም አቀፉ የፀረ ጾታዊ ጥቃት ቀን ጋር ተያይዞ ከህዳር 16 ጀምሮ በተለያየ መንገድ ንቅናቄ ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመው ይህም ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር እና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር እየተፈፀመ ያለውን ጾታዊ ጥቃት ለመከላከል መሆኑን አስገንዝበው ሁላችም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሀብተማርያም አለማየሁ እንደተናገሩት በሴቶችና ህጻናት ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ዘርፈ ብዙ በመሆኑ ድርጊቱን ለማስቆም ሁሉም ወደ ውስጡ ወስዶ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበው ሴቶች እርስ በእርሳቸው መተባበርና መከባበር አለባቸው ብለዋል፡፡
ሴቶች የተሳተፉበት ማንኛውም ተግባር ውጤታማ እንደሚሆንም ጠቁመው የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ ሁላችንም ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ ወ/ሮ ውባለም ታረቀኝ በበኩላቸው ከእሴታችን እየወጣን በመሆኑ ጾታዊ ጥቃት እየጨመረ መምጣቱን እና ጉዳዩን አቅልሎ የማየት እሳቤ እየተፈጠረ መሆኑን ገልፀው ድርጊቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ ድርጊቱን ለመከላከል ሁሉም በባለቤትነት ይዞ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
የሰላም እጦቱ ለጾታዊ ጥቃቱ መበራከት መንስኤ በመሆኑ ሰላም እንዲመጣ ለማድረግ በትኩረት ይዞ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበው ትውልድ ግንባታ እና እሴትን ማስቀጠል ላይ ትኩረት ሰጥተን በመስራት እያጋጠመ ያለውን ችግር መሻገር አለብንም ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል እየተሰራ ባለው ስራ የተሻለ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ህዳር 30 ቀን 2018 ዓ/ም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top