መምሪያው ከታህሳስ 03 እስከ ታህሳስ 06 እድሜያቸው ከ10 አመት በታች ለሆኑ ህጻናት የሚሰጠውን አራተኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደብረታቦር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀይለኢየሱስ ሰለሞን እንዳሉት የፖሊዮ በሽታ በህጻናት ላይ ከአካል ጉዳት እስከ ሞት እያደረሰ በመሆኑ በሽታውን ለመከላከል ክትባት በየጊዜው እየተሰጠ መሆኑን እና በባለፈው የተሰጠው ክትባት በጥሩ መንገድ መጠናቀቁን ገልፀው አሁን የሚሰጠውን የመከላከያ ክትባትም ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስኬድ ሁላችንም በትኩረት ይዘን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
ሁሉም ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት ይዘው ከሰሩ ክትባቱን በሚፈለገው መንገድ መስጠት እንደሚቻልም አስገንዝበው የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባቱን እና ሌሎችንም ተጓዳኝ የጤና ስራዎች በጥሩ መንገድ ለመፈፀም ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ የጤና ትምህርትና ኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ አዲሱ መኮንን ከፖሊዮ መከላከያ ክትባቱ ዘመቻ ጋር አያይዘው ሰነድ አቅርበዋል፡፡ የፖሊዮ በሽታ በዓይን በማይታዩ የፖሊዮ ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ በአይነ ምድር በተበከለ ምግብ ወይም ውሀ ወደ ጤነኛ ሰው የሚተላለፍ እና በዜጎች ላይ ከአካል ጉዳት እስከ ሞት እያደረሰ ያለ መሆኑን እና አንድ ህጻን በበሽታው ከተጠቃ ለ200 ህጻናት እንደሚያስተላልፍ ገልፀው በሽታውን ለመከላከል ለህጻናት ክትባት በዘመቻ ሲሰጠ መቆየቱን አውስተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የፖሊዮ በሽታ በአንዳንድ አካባቢዎች እየታየ በመሆኑ የሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የፖሊዮ መከላከያ ክትባት በዘመቻ የሚሰጥ መሆኑን አንስተው በክልላችን ብሎም በከተማ አስተዳደራችን ክትባቱ ከታህሳስ 03 እስከ ታህሳስ 06 እድሜያቸው ከ10 አመት በታች ለሆኑ ህጻናት እንደሚሰጥ አሳውቀዋል፡፡
ኦፊሰሩ አያይዘውም በከተማ አስተዳደሩ ለ39 ሽህ 281 ህጻናት የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥ ገልፀው ቤት ለቤት፣ በት/ቤትና በሌሎችም አመች ቦታዎች ክትባቱ እንደሚሰጥ ጠቁመው ከአሁን ቀደም ክትባቱን ቢከተቡም ባይከተቡም እድሜያቸው ከ10 አመት በታች ለሆኑ ህጻናት ክትባቱ እንደሚሰጥ ተናግረው የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባቱን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስኬድ ባለድርሻ አካላት በትኩረት ይዘው ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላትም በሰጡት ሀሳብ የፖሊዮ በሽታ ታክሞ መዳን የማይችል እና ትልቅ ጉዳት ያለው በመሆኑ በሽታውን ለመከላከል ህጻናትን በሚፈለገው አግባብ ማስከተብ እንደሚገባ ተናግረው የአሁኑን የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ውጤታማ ለማድረግ እና ህጻናት በአግባቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ሁላችንም ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን ብለዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ክትባቱን መከተብ ያለባቸው ህጻናት ት/ቤት ላይ የሚገኙ መሆናቸውንም ጠቁመው ህጻናቱ ክትባቱን በአግባቡ እንዲከተቡ ለማድረግ ት/ቤቶች በትኩረት ይዘው መስራት እንዳለባቸው እና ወላጆችም ልጆቻቸው ክትባቱን እንዲከተቡ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ ማርየ እንግዳየሁ እንደገለጹት የፖሊዮ በሽታ በህጻናት ላይ የአካል ጉዳትና ሞት የሚያስከትል መሆኑን ጠቅሰው በሽታውን ለመከላከል ህጻናትን መከተብ ዋናው መፍትሄ ስለሆነ ክትባቶች ሲሰጡ መቆየታቸውን አውስተው አሁንም የመከላከያ ክትባቱ በዘመቻ የሚሰጥ በመሆኑ ክትባቱን ውጤታማ ለማድረግ ሁላችንም በትኩረት ይዘን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ እየበሩ አእምሮ እንደተናገሩት ጤናማ የሆነ ትውልድን ለመገንባት ህጻናት ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ አንስተው የፖሊዮ በሽታ ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን እያደረሰ በመሆኑ በሽታውን ለመከላከል ሁሉም ህጻናት እንዲከተቡ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ቄስ መልካሙ ላቀው በበኩላቸው ዘርፈ ብዙ ጉዳት እያደረሰ ያለውን የፖሊዮ በሽታ ለመከላከል ህጻናት በአግባቡ እንዲከተቡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው የፖሊዮ ክትባት ዘመቻውን ውጤታማ ለማድረግ ሁላችንም በባለቤትነት ይዘን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
በተያያዘም የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ የማህፀን ጫፍ ካንሰርን እና የማርበርግ ቫይረስ በሽታን አስመልክቶ በንቅናቄ መድረኩ ለተገኙ ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ሰርቷል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ/ም
