የጥፋት ሀይሉ በደብረታቦር ከተማ በመንግስትና በግለሰብ ሀብት ንብረት ላይ ውድመት እና ዘረፋ መፈፀሙን ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡

የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን እንደገለጹት ከተመዋን የማውደም ተልእኮ ይዞ የመጣው ወራሪ ሀይል የውጭ ጠላቶች ያደርጉታል ተብሎ በማይታሰብ ደረጃ የመንግስትና የግለሰብ ሀብት ንብረት ላይ ውድመት እና ዘረፋ መፈፀሙን ጠቅሰው ብዛት ያላቸው የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት፣ የደቡብ ጎንደር ዞን እና የፋርጣ ወረዳ ተቋማት በእሳት እንዲቃጠሉ ማድረጉን እንዲሁም በውስጣቸው ያለው የኤሌክትሮኒክስ እቃ እና ሌሎችም ቁሳቁሶች እንዲወድሙና እንዲበላሹ አድርጓል ብለዋል፡፡
የእናቶችን አምቡላንስ እና ሌሎችንም ተሸከርካሪዎች በማቃጠል እኩይ ተግባር መፈፀሙን እንዲሁም ለእናቶችና ህጻናት የሚሆን መድሀኒትም እንዲቃጠል ማድረጉን ገልፀው የግለሰብ ቤትን የማቃጠል፣ ሀብት ንብረት የማውደምና የመዝረፍ ድርጊት መፈፀሙንም ጠቁመው ቡድኑ የፈፀመው ድርጊት ምግባሩን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከንቲባው አያይዘውም ታጣቂ ቡድኑ ከተመዋን ለማውደም በርካታ ሀይሉን ይዞ ቢመጣም ከተመዋን እንዳይቆጣጠር ሕዝቡ ከመንግስት ጎን ሁኖ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተው በክልሉ የፀጥታ ሀይል፣ በከተማ አስተዳደሩ ፖሊስና ሚሊሻ እንዲሁም በደቡብ ጎንደር የፀጥታ ሀይል ቅንጅትና ቁርጠኝነት ወራሪ ሀይሉ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ መመለሱን እና ከተመዋንና ነዋሪውን መታደግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
ከትናንት አመሻሽ ጀምሮ ከተመዋ ፍጹም ሰላም መሆኗንም ገልፀው የቀደመ አይነት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን እና የንግድ ድርጅቶችና ሌሎችም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰው በከተመዋ የነበረውን መነቃቃት ለማስቀጠል ይሰራልም ብለዋል፡፡
በወራሪ ሀይሉ የወደሙትን ተቋማት በማስተካከል እና የመጠቀሚያ ቁሳቁሶችንም በመማሟላት ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ለማድረግ በትኩረት ተይዞ እንደሚሰራም የገለጹት ከንቲባው ቢሮዎቹን ለመገንባት እና ቁሳቁሶችን ለማሟላትም ማህበረሰቡ መተባበር እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
የጥፋት ሀይሉ የሚያስመልሰው ምንም አይነት የሕዝብ ጥያቄ ባለመኖሩ ማውገዝና ይበቃል ማለት እንደሚገባም ተናግረው ህብረተሰቡ ሰላሙን ለማስጠበቅ መስራት እንዳለበት አስገንዝበው ሰላም የሁሉም ጉዳይ መሰረት በመሆኑ ስለ ሰላም ሁላችንም ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
በውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ወገኖች ከተመዋ በታጣቂ ሀይሉ እንዳትያዝ ለማድረግ በተለያየ መንገድ ሲያግዙና ሲደግፉ እንደነበር አንስተው ለዚህም ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ለከተማችን መላው ሕዝብ እና ለሁሉም የፀጥታ ሀይል የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በተያያዘም የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር የስራ ሀላፊዎች በወራሪ ቡድኑ የወደሙትንና የተዘረፉትን የመንግስት ተቋማት፣ ሀብት ንብረት እና የግለሰብ ቤት፣ ሀብት ንብረት ምልከታ አድርገዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን የካቲት 05 ቀን 2018 ዓ/ም
