ነዋሪዎቹ የጥፋት ቡድኑ በከተመዋ በመንግስት ተቋማት፣ ሀብት ንብረት ላይ ያደረሰውን ውድመት እና የፈፀመውን ዘረፋ ምልከታ አድርገዋል፡፡

የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ የሰላም ጉዳይ ላይ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይቱ ላይ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን እንደገለጹት ከተመዋን ለመውደም እና ህዝቡን ለማንገላታት በርካታ ወራሪ ሀይል መምጣቱን አንስተው የውጭ ጠላቶች ይፈጽሙታል ተብሎ በማታሰብ ደረጃ መጠነ ሰፊ ውድመት እና ዘረፋ መፈፀሙን ጠቁመው ብዛት ያላቸው የመንግስት ተቋማት እንዲቃጠሉ ማድረጉን እና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ ተሸከርካሪዎችና ሌሎችም ቁሳቁሶች ማውደሙን እና መዝረፉን ጠቅሰው የግለሰብ ቤትን በማቃጠል ሀብት ንብረት እንዲወድም ማድረጉን እና የተለያዩ ነገሮችን መዝረፉንም ተናግረዋል፡፡
የጠላት ሀይል ከተመዋን በመቆጣጠር የተለያዩ አስከፊ ድርጊቶችን ለመፈፀም ቢመጣም ህዝቡ ከመንግስት ጎን ሁኖ ባደረገው ትልቅ አስተዋጽኦ እና የፀጥታ አካሉ ባደረገው የሞት የሽረት ትግል ወራሪው ሀይል አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ መመለሱንም አንስተው ህዝቡ ላደረገው አስተዋጽኦ እና የፀጥታ አካሉ ላሳየው ቁርጠኝነትና ተጋድሎ ከንቲባው ምስጋና አቅርበው አንዳንድ ግለሰቦች እየሰሩት ካለው የባንዳነት ስራ ሊቆጠቡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ከንቲባው አክለውም የጥፋት ቡድኑ የህወሀትና የሻቢያን ተልእኮ ለማስፈፀም እየሰራ ቢሆንም መቸም እንደማይሳካለት ጠቁመው ቡድኑ ድጋሜ እኩይ ድርጊት እንዳይፈጽም ለማድረግ በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበው የወደሙትን ተቋማት ገንብቶ ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ለማድረግ መተባበር እንደሚያስፈልግ ተናግረው የከተማችን ሰላም ለማስጠበቅ እና ልማትን ለማስቀጠል ተቀናጅተንና ተጋግዘን መስራት አለብንም ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ደበበ አክሎግ እንደተናገሩት ሀገራችን ወርሮ የነበረውን ጣሊያን ጨምሮ ሌሎችም የውጭ ጠላቶች ይህን ያህል ውድመትና ጥፋት አለመፈፀማቸውን አንስተው ወራሪው የጠላት ሀይል ግን ሴቶችን መድፈሩን፣ በርካታ የመንግስት ተቋማትን በእሳት ማቃጠሉን፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን እና ሌሎችንም ቁሳቁሶችን ማውደሙንና መዝረፉን ጠቅሰው የግለሰብ ቤትን በማቃጠል እንዲወድም ማድረጉን፣ ሀብት ንብረት መዝረፉን እና ከችግር ላይ እንዲወድቁ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
ህዝቡ ከመንግስት ጎን ሁኖ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረው መላው የፀጥታ አካል በጀግንነትና በቁርጠኝነት ትግል አድርጎ የመጣውን ወራሪ ሀይል አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት እንዲመለስ ማድረጉን አንስተው ለመላው ህዝብ እና ለሁሉም የፀጥታ አካል ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን አንዳንድ የጥፋት ቡድኑ ተላላኪ ግለሰቦች ያሉ በመሆናቸው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበው ይህ እኩይ ድርጊት ከተማችን ላይ እንዳይደገም ለማድረግ ሁላችንም መስራት አለብን ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙ ነዋሪዎችም በሰጡት ሀሳብ ወራሪ ሀይሉ በከተመዋ የፈፀመው ድርጊት ታሪክ ይቅር የማይለው መሆኑን ተናግረው እንዳይደገም ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ጠቁመው አኩሪ ተጋድሎ በማድረግ ከተመዋን ከጠላት ያዳነውን የፀጥታ አካል አመስግነዋል፡፡
ህወሀትና ሻቢያ ለብዙ አመታት ሲሰሩት የቆዩት ሴራ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ ከችግሩ ለመውጣት ነገሮችን በብስለት ማስኬድ እንደሚስፈልግም አንስተው የህግ የበላይነት እንዲከበር እና ሰላም እንዲረጋገጥ ለማድረግ በአንድነት መቆም እንደሚገባም ተናግረው ከዚህ በላይ ኪሳራ መድረስ ስለሌበት ሁላችንም ማውገዝና ይበቃል ማለት አለብን ብለዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን የካቲት 07 ቀን 2018 ዓ/ም
