የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የ2018 በጀት አመት ስድስት ወራት እቅድ አፈጻፀም ግምገማ መድረክ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የመምሪያው ምክትል ሀላፊ ወ/ሮ ያየሽ እሸቴ በተቋሙ በባለፉት ስድስት ወራት የተከናዎኑትን ተግባራት እቅድ አፈጻፀም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ የለውጥ ተግባራት በአግባቡ እንዲፈፀሙ ጥረት መደረጉን አንስተው የዘርፈ ብዙ ስራዎች እና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በጥሩ ሁኔታ መሰራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የንግድ ፍቃድ አገልግሎትን በአግባቡ ለማስኬድ፣ ገበያውን ለማረጋጋት፣ የህዝብ ክንፍ ስራዎችን ለማጠናከር፣ የመሰረታዊ ምርት አቅርቦትንና ስርጭትን በአግባቡ ለማስኬድ፣ የሸማቾችን ደህንነት ለማረጋገጥ፣ የነዳጅ አቅርቦትንና ስርጭትን የተሻለ ለማድረግ እንዲሁም ሌሎችንም ተግባራት በአግባቡ ለማከናዎን በትኩረት ተይዞ መሰራቱን አመላክተዋል፡፡
ምክትል ሀላፊዋ በቀጣይ የሚሰሩትን ስራዎች ያቀረቡ ሲሆን ስራዎችን በሚፈለገው መንገድ ለመፈፀም ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት ይዘው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበው ተቀናጅተንና ተጋግዘን በመስራት ተግባሮቻችን ውጤታማ በሆነ አግባብ ማከናዎን አለብንም ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላትም በሰጡት ሀሳብ ስራዎቻቸውን በተሻለ መንገድ ለመስራት ጥረት ማድረጋቸውን እና አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀው የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማህበረሰቡ ማቅረብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ህገወጥ ንግድን ለመከላከል እና ሁሉም የንግዱ ማህበረሰብ ህጋዊ ሁኖ እንዲሰራ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት በጋራ ሁነው ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመው የመሰረታዊ ምርት አቅርቦት አናሳ መሆኑን እና የመጣውንም በፍትሀዊነት ከማስራጨት አኳያ ክፍተት ያለ በመሆኑ ማስተካከል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ታድሎ ድረስ እንደገለጹት መድረኩ በተቋሙ ያሉትን ጥንካሬዎች ለማስቀጠል እና ክፍተቶችን ደግሞ ለመሙላት የጋራ እሳቤ የሚያዝበት መሆኑን አንስተው የንግድ ስርአቱን በአግባቡ ለማስኬድ እና የንግዱ ማህበረሰብን ለማጎልበት መስራት አለብን ብለዋል፡፡ የገበያ ማረጋጋቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከአጋር አካላት ጋር ተሁኖ እንደሚሰራም ገልፀው ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው የግብይት ማእከላትን ማስፋፋት እና የምርት ጥራትን ማረጋገጥ አለብንም ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ደበበ አክሎግ እንደተናገሩት የንግድ ስርአቱን በአግባቡ ማስኬድ እና መምራት ባለመቻል የሚፈጠረው ቀውስ ትልቅ በመሆኑ ከችግሩ ለመውጣት በትኩረት ይዞ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበው በዘርፉ የሚታየውን ህገወጥነት ለመከላከል በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር እና ገበያውን ለማረጋጋት እየተሰሩ ያሉትን ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበው የንግድ ስርአቱን ማዘመን እና የአገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮነን በበኩላቸው የንግድ ዘርፉ ብልሽት ከሚታይባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው የንግድ እንቅስቃሴውን በአግባቡ ለማስኬድ እና ህገወጥ የንግድ ስራን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ሁሉም የንግዱ ማህበረሰብ በህጋዊ መንገድ እንዲሰራ ለማድረግ እና እየታየ ያለውን ህገወጥነት ለማስቆም በትኩረት ይዞ መስራት እንደሚገባም ተናግረው የገበያ ማረጋጋቱን ስራ ለማገዝ እንደሚሰራ ገልፀው ተግባሩን በሚፈለገው መንገድ ለማስኬድ መስራት አለብንም ብለዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ጥር 28 ቀን 2018 ዓ/ም
