በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ስራ ፕሮጀክት ሁለተኛ ምዕራፍ የ2ኛ ዙር የአካባቢ ልማት ተጠቃሚዎች የምረቃ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡


የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ምግብ ዋስትናና ሴፍቲኔት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮኋንስ ካሴ እንደገለጹት 1 ሽህ 257 ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች በዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ ንዑስ ፕሮግራም ኑሯቸውን እንዲቀይሩ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል የተደረገላቸው የሴፍቲኔት የ2ኛ ዙር የአካባቢ ልማት ተጠቃሚዎች በዛሬው ዕለት ተመርቀዋል ብለዋል፡፡
ተመራቂዎች በተደረግላቸው ክትትል እና ድጋፍ ኑሯቸውን ለማሻሻል በከተማ ግብር እና በአካባቢ ጥበቃ ላይ በተለይም የከተማችን ጽዳትና ውበት በመጠበቅ ከተማችን አረንጓዴ እንድትሆን የሰሩት ስራ፣ የተቦረቦሩ መሬቶችን በማከም እና የቆሻሻ መጣያ ቦታዎችን በማጽዳት ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ እንዲሆኑ በማደረግ ውጤታማ ስራዎችን እንደሰሩ የገለጹት ኃላፊው ተመራቂዎች ከዚህ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ለመድረስ አሁንም ጠንክረው መስራት እንደሚገባቸው ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደበበ አክሎግ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በልማታዊ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው ተመራቂዎች ተመልሰው ወደ ድህነት እንዳይገቡ አሁን የያዙትን ሀብትና እውቀት በመጠቀም ወደተሻለ የኑሮ ደረጃ እንዲደርሱ ተከታታይ ድጋፍ እና ክትትል መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
በዕለቱ ከተመረቁ የሴፍቲኔት ተመራቂዎች መካከል በፕሮግራሙ መታቀፋቸው ያለማንም እርዳታ ልጆቻቸውን ማስተዳደር እንዲችሉ አቅም እንደፈጠረላቸው የገለጹት አስተያየት ሰጭዎች በፕሮግራሙ መታቀፋቸው የቁጠባ እና የሥራ ባሕላቸውን እንዳሳደገላቸው ገልፀው ለተጨማሪ የገቢ ማስገኛ የተሰጠነውን መሬት አሁንም ይዘን ብንቀጥል፣ የመስሪያና መሸጫ ቦታ ቢመቻችልን እና ቀጣይ ስራችን አስፍተን ለመስራት ብድር ቢመቻችልን የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡
በዕለቱም በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር የከተሞች ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ስራ ፕሮጀክት የ2ኛ ዙር እና ተጨማሪ ፋይናንስ የአካባቢ ልማት ተጠቃሚዎች ለከተማ አስተዳደሩ ስራና ስልጠና መምሪያ እና ለከፍለ ከተሞች ስራና ስልጠና ጽ/ቤቶች የሴፍቲኔት የተጠቃሚዎች የርክክብ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ጥር 28 ቀን 2018 ዓ.ም
