በምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከሚታቀፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ምልመላ ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ቅሬታዎችንና አቤቱታዎችን በአግባቡ መፍታት እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ፡፡

የደብረታቦር ከተማ ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ጽ/ቤት በአካባቢ ልማት እና ቀጥታ ድጋፍ ማእቀፍ የቅሬታና አቤቱታ አፈታት በተሻሻለው ጋይድ ላይን ዙሪያ ለቀበሌ ቅሬታ ሰሚ እና ለከተማ ቅሬታና አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
የደብረታቦር ከተማ ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ዮሀንስ ካሴ ስለ ቅሬታ ምንነት፣ ቅሬታ የሚቀርባቸውን መንገዶች፣ የቀበሌ እና የከተማ ቅሬታና አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ አደረጃጀት፣ ተግባርና ሀላፊነት እንዲሁም በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ስልጠናውን ሰጥተዋል፡፡ በየደረጃው የተቋቋመው ኮሚቴ በፕሮግራሙ በአካባቢ ልማትና በቀጥታ ድጋፍ ከሚታቀፉ ወገኖች ምልመላ ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ቅሬታዎችንና አቤቱታዎችን ተቀብሎ መፍትሄ የሚሰጥ መሆኑን አንስተው በተለያየ አግባብ ለሚቀርቡት ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በየቀበሌውና በከተማ ደረጃ የተቋቋሙት ኮሚቴዎች ከተለያዩ አደረጃጀቶች የተውጣጡ መሆናቸውንም ገልፀው ከፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ምልመላ ጋር ተያይዞ ለሚቀርቡት ቅሬታዎችና አቤቱታዎች መመሪያንና አሰራርን ተከትሎ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግም ጠቁመው ስራዎችን በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡
በስልጠናው ላይ የተሳተፉ አካላትም በሰጡት ሀሳብ የምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ለከተመዋና ለማህበረሰቡ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተው በርካታ ወገኖች በልተው እንዲያድሩ እያደረገ መሆኑን እና ሰርቶ መኖርን ያስተማረ ነው ብለዋል፡፡
በፕሮግራሙ የሚታቀፉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በፍትሀዊነት መመልመል እንደሚገባም ተናግረው የሚቀርቡትን ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ለመፍታት እየሰሩ መሆናቸውን እና አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀው በአካባቢ ልማት ላይ የሚሰሩ ወገኖችን ካለአግባብ የመጠቀም ሁኔታ በመኖሩ መስተካከል እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
በደብረታቦር ከተማ ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ጽ/ቤት የበጀትና እቅድ ዝግጅት ባለሙያ አቶ ጥላሁን ገብሩ እንደገለጹት ስልጠናው የኮሚቴ አባላትን አቅም በማጎልበት የሚቀርቡትን ቅሬታዎችና አቤቱታዎች በአግባቡ መፍታት እንዲችሉ መሆኑን አንስተው ከስልጠናው የተገኘውን ግብአት በተገቢው ሁኔታ በመጠቀም ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡
በፕሮግራሙ የታቀፉት የህብረተሰብ ክፍሎች ሰርተው ራሳቸውን እንዲለውጡ ለማድረግ ማገዝና መደገፍ እንደሚገባም አስገንዝበው በታችኛው የመንግስት አካል በፕሮግራሙ የተያዙትን ወገኖች ህግና አሰራር በማይፈቅደው መንገድ የመጠቀም ሁኔታ ያለ በመሆኑ መስተካከል አለበትም ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ዮሀንስ ካሴ የማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡ ሲሆን በፕሮግራሙ ከሚታቀፉት የማህበረሰብ ክፍሎች ምልመላ ጋር ተያይዞ የሚቀርቡትን ቅሬታዎችና አቤቱታዎች በአግባቡ መርምሮ መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
የፕሮግራሙን ተጠቃሚዎች በአግባቡ መያዝና መጠቀም እንደሚገባም ተናግረው አልፎ አልፎ የሚታዩትን ተገቢ ያልሆኑ አካሄዶች ማረምና ማስተካከል አለብንም ብለዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ጥር 23 ቀን 2018 ዓ/ም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top