ድንቅ ባህል ውብ ተፈጥሮ!!

ደብረታቦር ከተማ በ14ኛው ክፍለ ዘመን በ1327 ዓ/ም በአጼ ሰይፈ አርዕድ የተመሰረተች ስትሆን ለበርካታ አመታት የማዕከላዊ መንግስት መቀመጫ በመሆን አገልግላለች። ተስማሚ የአየር ንብረትን ከጣና እና ከጉና አዋህዳ የምትመግብ ሲሆን የአየር ንብረት ተስማሚነቷና ተፈጥሯዊ አቀማመጧ ለረጅም አመታት የማዕከላዊ መንግስት መቀመጫ እንድትሆን ተመራጭ አድርጓታል።
በዘመነ መሳፍንት ወቅት ለመሳፍንቶች ተመራጭ ከተማ እንደነበረች የታሪክ ድርሳናት የሚያስረዱ ሲሆን ከዘመነ መሳፍንት መክሰም በኋላም ታላቁ ንጉስ አጼ ቴዎድሮስ በዋና ከተማነት መርጠው መዲናቸው አድርገው ተጠቅመውባታል።
ደብረታቦር የብዙ ነገስታቶች መዲና የነበረች ከተማ መሆኗን አሁንም ድረስ የሚገኙት የቤተመንግስታት ፍርስራሾች ምስክር ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል የአጼ ሱሲኒዮስ አሪንጎ ቤተመንግስት፣ የአጼ ሰርፀድንግል ማህደረ ማርያም ቤተመንግስት፣ የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ አንገት እዳ ቤተመንግስት እና የአጼ ዮሀንስ 4ኛ ሰመርንሀ ቤተመንግስት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ቱባ ባህል፣ ሰፊ ታሪክ፣ ውብ ተፈጥሮ ያደላት ደብረታቦር ታህሳስ 29 የገና በዓልን በታላቁ ደብር ርእሰ አድባራት ደብረታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ባማረ መንገድ በማክበር በከተመዋ የሚከበሩት በርካታ በዓላት መከበር የጀመሩ ሲሆን በተንጣለለው አጅባር ሜዳ ላይ ጥር 11 የጥምቀት በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡
ከጥምቀት ቀጥሎ ባሉት ቀናትም በዓላት በጥሩ መንገድ እየተከበሩ የሚገኙ ሲሆን እስከ ጥር 29 በየቀኑ በሚባል ደረጃ በርካታ ሐይማኖታዊ በዓላት የሚከበሩባት ብቸኘዋ ከተማ ናት፡፡ ይህም ለከተመዋ የተሰጣት ትልቅ ገፀ በረከት ነው፡፡
በቀድሞ ዘመን የውጭ ሀገራት በሚፈጥሩት ተጽዕኖ በተለይም ከጣሊያን ጋር የነበረውን የህዝብ ተጋድሎ የሚዘክረውና ዘመናትን ያስቆጠረው በቡድን ተከፋፍለው በልምጭ /ስሚዛ/ እንጨቶች የሚከናወነው የፈረስ ጉግስ ፍልሚያም የከተማዋ የቆዬ መገለጫ ባህል ነው።
የፈረስ ጉግሱ የሰመዓቱ ቅዱስ መርቆሪዮስ ንግስ በዓል ጊዜ የሚካሄድበት ምክንያት ሰመዓቱ ቅዱስ መርቆሪዮስ ፈረሰኛ በመሆኑ እና የቤተክርስቲያን ጠላቶችን በፈረስ ጉግስ ይዋጋ የነበረ መሆኑን ለማስታዎስ ነዉ፡፡ ለአብነት ያክል ወላኒዎስ የተባለ ግለሰብ ቤተክርስቲያን የሚያፈርስና የሚበጠብጥ የነበረ ሲሆን ጥር 25 ተወግቶ በፈረስ እንዲጠቀጠቅ አድርጓል፡፡ ይሄው የፈረስ ጉግስ ባህላዊ ትይንት ብቻ ሳይሆን የሐይማኖታዊ ተጋድሎ መገለጫም እንደሆነ ይነገራል፡፡
የፊታችን ጥር 25 በጥንታዊቷ እና ታሪካዊቷ ደብረታቦር ከተማ ውብ በሆነው አጅባር ሜዳ ላይ የሰማእቱ ቅዱስ መርቆሪዮስ አመታዊ ክብረ በዓል በደማቅ ሁኔታ የሚከበር ሲሆን የፈረስ ጉግሱም ቀልብን በሚስብ መልኩ ይካሄዳል፡፡
በመሆኑም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የምትኖሩ ወገኖቻችን ጥር 25ን በተንጣለለው አጅባር ሜዳ በመገኘት በደማቅ ሁኔታ የሚከበረውን የቅዱስ መርቆሪዮስ በዓል እንድታከብሩ እና ባማረ መንገድ የሚካሄደውን የፈረስ ጉግስ እንድትታደሙ ተጋብዛችኋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ጥር 15 ቀን 2018 ዓ/ም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top