ደብረታቦር በ1327 ዓ/ም በአጼ ሰይፈ አርእድ የተመሰረተች ጥንታዊት እና ታሪካዊት ከተማ ስትሆን ለብዙ አመታት የነገስታት መቀመጫ የሆነች እና በአፍሪካ የቴክኖሎጅ መነሻ ከተማ ናት፡፡
ደብረታቦር እና አካባቢው በርካታ ሰው ሰራሽ፣ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ የቱሪስት መስህብ ሀብት የሚገኝበት ነው፡፡ ጥር ወርን ደግሞ ከተመዋ እና አካባቢው በሐይማኖታዊ በዓላት ደምቀው እያሳለፉ ናቸው፡፡

በከተመዋ ከታህሳስ 29 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የተለያዩ ሐይማኖታዊ በዓላት በመንፈሳዊ ስርአት እና በባህላዊ ጨዋታዎች ደምቀውና አምረው የተከበሩ ሲሆን እስከ ጥር 29 ባሉት ቀናትም በርካታ ሐይማኖታዊ በዓላት ውብ በሆነው አጅባር ሜዳ ላይ በደማቅ ሁኔታ መከበራቸውን ይቀጥላሉ፡፡
በተለይም ጥር 25 የሚከበረው የሰማእቱ ቅዱስ መርቆሪዮስ ክብረ በዓል እና የሚካሄደው ሳቢና ማራኪ የፈረስ ጉግስ ደስታን የሚፈጥር እና ሀሴትን የሚያጎናጽፍ ነው፡፡ በከተመዋ ለዘመናት የቅዱስ መርቆሪዮስን ክብረ በዓል ምክንያት አድርጎ ሲካሄድ የቆየው የፈረስ ጉግስ አሁንም ሞቅ ደመቅ ብሎ ይካሄዳል፡፡
በመሆኑም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የምትኖሩ ወገኖች ጥር 25 በደብረታቦር ከተማ አጅባር ሜዳ ላይ ተገኝታችሁ የሰማእቱን ቅዱስ መርቆሪዮስ ክብረ በዓል እንድታከብሩ እና ሳቢና ማራኪውን የፈረስ ጉግስ እንድትታደሙ በአክብሮት ተጋብዛችኋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ጥር 14 ቀን 2018 ዓ/ም
