የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ከባለድርሻና አጋር አካላት ጋር የ2018 በጀት አመት የመጀመሪያውን ግማሽ አመት እቅድ አፈጻፀም ግምገማ መድረክ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የጽ/ቤቱ በጀትና እቅድ ዝግጅትና ክትትል ባለሙያ አቶ ያምራል አለሜ በግማሽ አመቱ የተከናዎኑትን ተግባራት እቅድ አፈጻፀም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በአጭር ጊዜ፣ በመካከለኛ ጊዜና በረዥም ጊዜ የሚፈቱ ጉዳዮችን በመለየት መፍትሄ እንዲሰጣቸው መሰራቱን ገልፀው ለከንቲባ ኮሚቴ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን አዘጋጅቶ በማቅረብ ውሳኔ እንዲሰጥ ሲደረግ መቆየቱንም ጠቅሰዋል፡፡
የግልፀኝነትንና የተጠያቂነትን አሰራር ለማስፈን ከሙስና መከላከል ጋር ተያይዞ ለቀረቡ ጥቆማዎች አስተዳደራዊና ህጋዊ መፍትሄ እንዲሰጥ መደረጉን እንዲሁም በተለያየ አግባብ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መሰራቱን ገልፀው ተቋማዊ የለውጥ ሰራዊት ግንባታን ለማጠናከር እና የዘርፈ ብዙ ተግባራትን በአግባቡ ለማስኬድ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡
ባለሙያው በተቋሙ ያሉትን ቡድኖች እና የክፍለ ከተሞችን እቅድ አፈጻፀም ሪፖርትንም ያቀረቡ ሲሆን ስራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተሰሩ መሆናቸውን አንስተው ተግባራትን በሚፈለገው መንገድ ለመፈፀም በትኩረት ይዘን ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላትም በሰጡት ሀሳብ በተቋሙ እና በየክፍለ ከተሞቹ ስራዎች በተሻለ መንገድ መሰራታቸውን አንስተው ተሰሩ የተባሉትን ስራዎች ታች ወርዶ በተጨባጭ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረው በቀጣይም ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል እና ክፍተቶችን ለማስተካከል እንሰራለን ብለዋል፡፡
የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እና ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መስራት እንደሚገባም ጠቁመው የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር ስራዎችን በአግባቡ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀው ለክፍለ ከተሞች ምቹ የስራ ሁኔታ መፈጠር እንዳለበትም ጠይቀዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ፕላንና ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ እሸቱ ውለታው እንዳሉት ተግባራትን በጥሩ መንገድ ለማከናዎን በትኩረት ይዞ መስራት እንደሚገባ ተናግረው እያጋጠመ ያለውን የቁሳቁስና የግብአት አለመሟላት በመተጋገዝና በመደጋገፍ መፍታት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ያለውን አቅም በመረዳት ያሉትን ምቹ ሁኔታዎች ተጠቅሞ ስራዎችን በተሻለ ሁኔታ ለመስራት ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አንስተው ችግሮችን ለመሻገር እና ከተመዋን በሚፈለገው መንገድ ለማስኬድ በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበው ስራዎችን በቅንጅትና በትብብር መስራት አለብንም ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አወቀ ፍሌ እንደተናገሩት ተግባራትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመፈፀም በትኩረት ተይዞ ሲሰራ መቆየቱን እና በርካታ ተግባራት መከናዎናቸውን ገልፀው ያሉትን ጥንካሬዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እና ክፍተቶችን ደግሞ መሙላት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ለመስጠት የተደረገው ጥረት አበረታች መሆኑንም ጠቁመው የሚፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በአግባቡ ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው ስራዎችን በሚፈለገው መንገድ ለመስራት ተቀናጅተንና ተጋግዘን መስራት አለብንም ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በግማሽ አመቱ የተሻለ አፈጻፀም ላላቸው ክፍለ ከተሞች፣ የጽ/ቤቱ ቡድኖችና ባለሙያዎች እውቅና ተሰጥቷል፡፡
በመጨረሻም የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አወቀ ፍሌ እና የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ፕላንና ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ እሸቱ ውለታው ርክክብ አድርገዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ጥር 13 ቀን 2018 ዓ/
