በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በደብረታቦር ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ፡፡

በከተመዋ የ2018 ዓ/ም የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምት በዓል በአጅባር ጥምቀተ ባህር በሐይማኖታዊ ክንዋኔዎች በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡
በበዓሉ አከባበር ላይ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን፣ የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ምህረት ሞላ፣ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ደበበ አክሎግ፣ የደብረታቦር ከተማ ቤተክነት ስራ አስኪያጅ በትረ ትጉሀን ሁልጊዜ አለማየሁ፣ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አቶ አለበል ደመላሽ እንዲሁም ሌሎች የሐይማኖት አባቶች ተገኝተዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን በበዓሉ አከባባር ላይ ባስተላለፉት መልእክት እንዳሉት የጥምቀት በዓል ጌታችን መዳኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁን በማሰብ የሚከበር ታላቅ ሐይማኖታዊ በዓል መሆኑን አንስተው እኛም በዓሉን ስናከብር ሐይማኖታዊ ስርአቱን ጠብቀን የሰው ልጅ ከሀጢያት ወደ መንፈሳዊ ህይዎት እንዲመለስ በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመደጋገፍ፣ በይቅርታና ምህረት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በዓለ ጥምቀት እና ትህትና ተነጣጥለው የሚታዩ ባለመሆናቸው አሁን ያለነው ትውልዶች ይህን ሐይማኖታዊ አስተምሮ ተቀብለን ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለመቻቻል፣ ለመረዳዳት፣ ለመከባበር፣ ለልማት እንዲሁም ዝቅ ብለን ለማገልገል የተሰጠን ታላቅ ገፀ በረከት በመሆኑ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባልም ብለዋል፡፡
ከንቲባው አያይዘውም የከተመዋ ውበት በሆነው አጅባር ሜዳ ከጥምቀት ጀምሮ በርካታ ሐይማኖታዊ በዓላት የሚከበሩ መሆናቸውን ጠቅሰው በዓላቱ በተከታታይ ቀናት የሚከበሩ በመሆናቸው ለበዓላቱ ድምቀት እያንዳንዳችን የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡ ጥር 25 የሚከበረው የቅዱስ መርቆሪዎስ ክብረ በዓል ከእስካሁኑ በበለጠ መንገድ እንዲከበር እና የፈረስ ጉግሱም ለየት ባለ መልኩ እንዲካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልፀው ሁነቱ የህዝቡን አንድነት የሚያፀና እና ህዝባዊ ትስስርን የሚያጠናክር በመሆኑ እንዲሁም የከተማችን ገጽታ ለመገንባት እና የቱሪዝሙን እንቅስቃሴ ለማጠናከር የሚረዳ በመሆኑ በላቀ መንገድ እንዲካሄድ ሁላችንም ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ምህረት ሞላ በትናትናው እለት በነበረው መርሀ ግብረ እንዳሉት የጥምቀት በዓል የሰው ልጆች የእዳ ደብዳቤ የተቀደደበት፣ ከመከራና ስቃይ ወጥተው ነጻነት የተጎናፀፉበት እና ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ከጨለማ አውጥቶ ወደ ብርሀንና እውነተኛ ብርሀን የወሰደበት መሆኑን ገልፀው በዓሉ የመንጻት፣ የመቀደስ፣ የመባረክና ጥሩ ድርጊት የሚፈፀምበት በመሆኑ ምእመናንም ጥሩ ነገሮችን መስራት፣ መከባበር፣ መተሳሰብና መደጋገፍ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በአሁኑ ዘመን ብዙ መልካም ያልሆኑ ነገሮች እየተፈፀሙ ያሉበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቅሰው መጥፎ ድርጊት ከመፈፀም እና ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን ከመስራት መቆጠብ እንደሚገባም አሳስበው ፈጣሪ ለሰው ልጆች ሁሉ መልካሙን ነገር እንዲያደርግ ተመኝተው የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓልን በሰላም፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብና በአንድነት ማክበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በዓሉን ያከበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችም በሰጡት ሀሳብ የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓልን በጥሩ መንፈስና በታላቅ ደስታ ማክበራቸውን ገልፀው በዓሉን ስናከብር ቂምና ጥላቻን ትተን በእርቅና በመተሳሰብ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመው በችግር ላይ የሚገኙ ወገኖችን መደገፍና ማገዝ እንደሚያስፈልግ ተናግረው ለሰላምና ለአንድነት ሁላችንም መስራት አለብን ብለዋል፡፡
በበዓሉ አከባበር ላይ በመንበረ ብርሀን እናቲቱ ማርያም ቤተክርስቲያን ሐይማኖት አባቶች መሪነት የተለያዩ መንፈሳዊ መርሀ ግብሮች የተካሄዱ ሲሆን ትምህርተ ወንጌልና ሌሎችም ክንዋኔዎች ተፈጽመዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ጥር 11 ቀን 2018 ዓ/ም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top