በኢፌዴሪ ስራና ክህሎት ሚኒሰትር አስተግባሪነት በአለም ባንክ የበጀት ድጋፍ የደብረታቦር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ፣ ከኢንዱስትሪዎች እና ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በመግባቢያ ሰነዱ ስምምነት የጋራ ስራዎችና ትስስር ላይ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እና የኮሌጁ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ደሴ መኮንን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዜጎችን በእውቀትና በክህሎት ለማበልፀግ የተሰጣቸውን ተልእኮ በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበው ጥሩ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ወጣቶችን በማፍራት ራሳቸውን እንዲለውጡ እና ማህበረሰባቸውን እንዲጠቅሙ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ያሉት ኢንዱስትሪዎች ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር እየተደረገ ላለው እንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ መሆናቸውን አንስተው ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ባሉት ኢንዱስትሪዎች ላይ በተገቢው ሁኔታ በመስራት ውጤታማ መሆን እንደሚያስፈልግም አስገንዝበው የጋራ ስምምነት ሰነዱ ስራዎችን መልክ ባለው መንገድ ተጋግዞ ለመስራት የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
የደብረታቦር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አሰልጣኝ እና በኮሌጁ የአለም ባንክ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ቢሆን ጉበና በዩኒቨርሲቲውና በኮሌጁ ትብብር መሰራት ያለባቸውን ጉዳዮች አስመልክተው ሰነድ አቅርበዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጁ ለኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልግ የሰው ሀይል መገንባት፣ በውድድር ላይ የተመሰረተ ስልጠና መስጠት፣ ችግር ፈች ጥናትና ምርምር ስራ መስራት እና ሌሎችም ተያያዥ ሀላፊነቶች ያሏቸው መሆኑን ጠቅሰው ተግባሮቻችን በትብብር መፈፀም አለብን ብለዋል፡፡ የስምምነት ሰነዱ የፈጠራ ስራዎችን ለመስራት፣ ጠቃሚ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለመስራት፣ የቴክኖሎጅ ሽግግር ለማድረግ፣ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ለመስጠት፣ ለምሩቃን የስራ እድሎችንን ለማመቻቸት፣ ኢንዱስትሪን ለማስፋት እና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ መሆኑን ገልፀው ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ተቀናጅተንና ተባብረን መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጅ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ታደሰ ዋለልኝ በበኩላቸው ከስምምነቱ ጋር አያይዘው ሰነድ አቅርበዋል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መማር ማስተማር፣ ጥኛትና ምርምር ማድረግ እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት ተልእኮዎች ያሏቸው መሆኑን ገልፀው ዩኒቨርሲቲውም በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የስምምነት ሰነዱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ አግኝቶ ለመጠቀም፣ ጥሩ እውቀትና ክህሎት ያላቸውን ዜጎች ለማፍራት፣ ምሩቃንን ለማብቃት፣ ችግር ፈች ጥናትና ምርምር ለመስራት፣ የቴክኖሎጅ ሽግግር ለማድረግ፣ ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ፣ የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣትና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰው ትብብራችንን አጠናክረን ማስቀጠል አለብን ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላትም በሰጡት ሀሳብ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት እና ዜጎች በእውቀትና በክህሎት የበለፀጉ ለማድረግ ሁለቱ ተቋማቱ ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው አንስተው ዩኒቨርሲቲው ኮሌጁን በተለያየ መንገድ እያገዘ በመሆኑ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ወጣቶች በየተማሩባቸው የትምህርት ዘርፎች እና በየሰለጠኑባቸው የሙያ መስኮች ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት ይዞ መስራት እንደሚገባ ተናግረው የጋራ ስምምነቱ ተቋማቱ ስራዎችን በጥሩ መንገድ እንዲሰሩ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራልም ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተወካይ ዲን አቶ ክንዴ ጌታሁ እንደገለጹት የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ለኮሌጁ ትልቅ ባለውለታ መሆኑን አንስተው በእውቀትና በክህሎት የበቁ ወጣቶችን ለመፍጠር ተቋማቱ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን እና አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት መምሪያ ሀላፊ እና የኮሌጁ ስራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ስማቸው አገኝ እንደተናገሩት ተቋማቱ የተሻለ ዜጋን ለመፍጠር መስራት የሚጠበቅባቸው መሆኑን ጠቁመው የጋራ ስምምነት ማድረጋቸው ያለውን የእውቀትና የክህሎት ክፍተት በመሙላት ውጤታማ ስራዎችን ለማስራት ይረዳል ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ሀብቴ አለማየሁ በበኩላቸው ሰልጣኞችና ምሩቃን ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲው እና ኮሌጁ ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው አንስተው በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን እና ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀው በተነጋገርንበት ልክ ተግባራትን በአግባቡ መፈፀም አለብን ብለዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ጥር 07 ቀን 2018 ዓ/ም
