የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን በማሳለጥ የዜጎችን ህይዎት መታደግ እና ሀብት ንብረትን ከጉዳት ማዳን እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት /ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር 2018 በጀት አመት ስድስት ወራት እቅድ አፈጻፀም ግምገማ እና በመንገድ ትራፊክ ደህንነት ላይ የስልጠና መድረክ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የጽ/ቤቱ እቅድና በጀት ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ባለሙያ አቶ የኔነው ማሩ 2018 በጀት አመት ስድስት ወራት የተሰሩትን ተግባራት እቅድ አፈጻፀም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ በግማሽ አመቱ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መሰራቱን፣ ተሸከርካሪዎችን የመቆጣጠርና የመከታተል ስራ መሰራቱን፣ ለማህበረሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሸከርካሪዎች ስምሪት መሰጠቱን፣ የውስጥና የውጭ ቁጥጥር ስራዎች መሰራታቸውን፣ ወደ ተቋሙ የሚሄዱ ተገልጋዮችን የማስተናገድ ስራ መሰራቱን፣ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ለመፍታት ጥረት መደረጉን እና ሌሎችም ተግባራት መፈፀማቸውን ገልፀዋል፡፡

በርካታ የበጎ ፈቃድ ተግባራት መከናዎናቸውንም ጠቅሰው በቀጣይ ጊዜያት ስራዎችን በተሻለ መንገድ ለማከናዎን ሁላችንም በትኩረት ይዘን መስራት አለብን ብለዋል፡፡

በጽ/ቤቱ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ክትትልና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ታድሎ ድረስ ከመንገድ ትራፊክ ደህንነት አኳያ የተጠና ጥናት ያቀረቡ ሲሆን የትራፊክ አደጋ ለብዙ ወገኖች ህይዎት መጥፋት ምክንያት እየሆነ እና በርካታ ጉዳቶችን በማድረስ ላይ እንደሚገኝ ገልፀው የመንገድ ምቹ አለመሆን፣ ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር፣ ከመጠን በላይ ጠጥቶ ማሽከርከር እና ሌሎችም ጉዳዮች ለትራፊክ አደጋ መበራከት መንስኤ መሆናቸውን ጠቅሰው ከችግሩ ለመውጣት ፍጥነትን መቀነስ፣ ርቀትን ጠብቆ ማሽከርከር፣ ለእግረኛ ቅድሚያ መስጠት እና ሌሎችንም ህጎች አክብሮ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የትራፊክ ፖሊሶች እና የትራንስፖርት ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች የትራፊክ ፍሰቱን በአግባቡ በማሳለጥ እየደረሱ ያሉትን የትራፊክ አደጋዎች ለማስቀረት በትኩረት ይዘው ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላትም በሰጡት ሀሳብ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በሰሩት ስራ ባለፈው አመት ስራዎችን በጥሩ መንገድ መፈፀም መቻሉን አንስተው በዚህ አመት ስድስት ወራት የተሰሩት ስራዎችም የተሻሉ መሆናቸውን እና አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ተግባራትን ወጥ በሆነ መንገድ ማከናዎን እንደሚያስፈልግ እና ትርፍ መጫንን ለማስቀረት ህብረተሰቡ ማገዝና መተባበር እንዳለበትም ገልፀው ስራዎችን በሚፈለገው አግባብ ለመፈፀም በትኩረት ይዘው እንደሚሰሩ ተናግረው ሁላችንም በባለቤትነት ይዘን ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት /ቤት ሀላፊ አቶ አዳነ ደምሴ እንደገለጹት በባለፈው በጀት አመት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው በመስራታቸው ተግባራትን በጥሩ ሁኔታ መፈፀማቸውን አስታውሰው በተያዘው በጀት አመትም እስካሁን ባለው ጊዜ ስራዎች በተሻለ መንገድ መሰራታቸውን እና ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል፡፡

ከልክ በላይ መጫንን ለማስቆም ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አንስተው ከችግሩ ለመውጣት የማህበረሰቡን አስተሳሰብ መቀየር አስፈላጊ በመሆኑ የግንዛቤ ፈጠራን ቀጣይነት ባለው መንገድ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበው ስራዎቻችን ውጤታማ ለማድረግ በባለቤትነት ይዘን መስራት አለብንም ብለዋል፡፡

የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን እንደተናገሩት ተቋሙ በባለፈው በጀት አመት ጥሩ አፈጻፀም እንደነበረው እና አርእያነት ያለው ስራ መስራቱን አስታውሰው ያለውን ጥንካሬ ማስቀጠል እና ክፍተቶችን ደግሞ ማስተካከል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ህገወጥ ተሸከርካሪዎችን መልክ ለማስያዝ እና ትርፍ የሚጭኑትንም ለማስተካከል በተገቢው ሁኔታ መቆጣጠር እንደሚገባም አስገንዝበው ተግባራትን በቅንጅትና በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ሁላችንም በትኩረት ይዘን መስራት አለብን ብለዋል፡፡

 

  ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ታህሳስ 23 ቀን 2018 .

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top