የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት የፊታችን ጥር 25 የሚከበረው የቅዱስ መርቆሪዮስ ክብረ በዓል በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር እና የፈረስ ጉግሱም በላቀ መንገድ እንዲካሄድ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱ ላይ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አለበል ደመላሽ ከቅዱስ መርቆሪዮስ ዓመታዊ ክብረ በዓል አከባበር እና ከፈረስ ጉግሱ ጋር አያይዘው ሰነድ አቅርበዋል፡፡ የቅዱስ መርቆሪዮስ ክብረ በዓል እና የፈረስ ጉግስ ከጥንት ጀምሮ ትውፊቱን በጠበቀ መንገድ እየተከበረ መሆኑን እና የባለፈው ዓመት ክብረ በዓል እና የፈረስ ጉግስም በጥሩ ሁኔታ መካሄዱን አስታውሰው የዚህን ዓመት የቅዱስ መርቆሪዮስ ክብረ በዓል እና የፈረስ ጉግስንም ከፍ ባለ ደረጃ ለማስኬድ ሁሉም አካል በባለቤትነት ይዞ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
በከተመዋ ከታህሳስ 29 ጀምሮ እስከ የካቲት አጋማሽ ድረስ በርካታ በዓላት የሚከበሩ መሆናቸውንም ጠቅሰው በዓላቱ በደማቅ ሁኔታ እንዲከበሩ ለማድረግ በትኩረት ይዞ መስራት እንደሚገባ ተናግረው የቅዱስ መርቆሪዮስ ዓመታዊ ክብረ በዓል እና የፈረስ ጉግሱ በጥሩ ሁኔታ እንዲካሄድ ማድረግ ቱሪዝሙን በማነቃቃት የገቢ ምንጭ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ሀላፊው አያይዘውም በዓሉ ህዝባዊ በዓል በመሆኑ በላቀ ደረጃ እንዲከበር ለማድረግ መላው ህዝብ በባለቤትነት ይዞ ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበው ለበዓሉ አከባበር ከአሁኑ ስራዎችን በአግባቡ ለመስራት አብይ ኮሚቴና ንኡስ ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ገልፀው ኮሚቴዎቹ በዓሉ እስከሚከበርበት ድረስ ተግባራትን በተገቢው ሁኔታ መፈፀም እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙ አካላትም በሰጡት ሀሳብ የቅዱስ መርቆሪዮስ ክብረ በዓል ከእስካሁኑ በበለጠ ሁኔታ እንዲከበር እና የፈረስ ጉግስም ከፍ ባለ ደረጃ እንዲካሄድ ለማድረግ ከአሁኑ የቅድመ ዝግጅት ስራ መጀመሩ ጥሩ መሆኑን አንስተው ስራዎችን በአግባቡ ለመስራት መቀናጀትና መናበብ እንደሚገባም ተናግረው ከፋርጣ ወረዳ፣ ከደቡብ ጎንደር ዞንና ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር ተቀራርቦ መሰራት አለበትም ብለዋል፡፡
በከተመዋ ከገና ጀምሮ በርካታ በዓላት የሚከበሩ በመሆናቸው ትልቅ ፀጋ መሆኑን ጠቁመው ያሉትን በዓላት በአግባቡ አልምቶ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባም ገልፀው ከተለያዩ አካባቢዎች መጥተው የቅዱስ መርቆሪዮስ ዓመታዊ ክብረ በዓልን እና የፈረስ ጉግሱን እንዲታደሙ ለማድረግ ሰላምና ፀጥታን ማረጋገጥ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
በውይይቱ ተሳታፊዎች ለተነሱት የተለያዩ ሀሳቦችም የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አለበል ደመላሽ መልስና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የቅዱስ መርቆሪዮስ ክብረ በዓል ከእስካሁኑ በበለጠ መንገድ እንዲከበር እና የፈረስ ጉግስም ከፍ ባለ ደረጃ እንዲካሄድ ለማድረግ ሁሉም አካል በባለቤትነት ይዞ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበው ከፋርጣ ወረዳ፣ ከደቡብ ጎንደር ዞንና ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡
የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ምህረት ሞላ እንደተናገሩት ደብረታቦርና ደቡብ ጎንደር በርካታ ፀጋዎች ያሉት አካባቢ በመሆኑ እነዚህን ፀጋዎች በአግባቡ ማስተዋወቅ እንደሚገባ ጠቁመው የቅዱስ መርቆሪዮስ ክብረ በዓል እና የፈረስ ጉግሱ መንፈሳዊና ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መንገድ ለማክበር ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖች ወደ ከተመዋ መጥተው በዓሉን እንዲያከብሩ እና የፈረስ ጉግሱን እንዲታደሙ ለማድረግ ሰላምና ፀጥታውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም አንስተው ለከተመዋ ውበት የሚሰጡ እና ገጽተዋን የሚያሳምሩ ስራዎችን መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ታህሳስ 15 ቀን 2018 ዓ/ም
