በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) በደብረታቦር ከተማ የሚሠሩትን የልማት ፕሮጀክቶች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ፣ የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮነን እና የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔን ጨምሮ ሌሎች መሪዎችም ተገኝተዋል።
የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮነን በሰጡት አስተያየት በከተመዋ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በጥሩ ኹኔታ እየተፈጸሙ መኾኑን ገልጸዋል።
ለደቡብ ጎንደር ዞን ጭምር አገልግሎት የሚሰጠው የኤሌክትሪክ ሰብስቴሽን በታለመለት ጊዜ ተጠናቅቆ አገልግሎት እየሰጠ መኾኑንም ጠቅሰዋል። ለኢንዱስትሪ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረትም ስለተቀረፈ ባለሃብቶች በከተመዋ ማልማት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታው 70 በመቶ መድረሱን እና በተያዘለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል። ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር የሚሠራ ባለ 720 አልጋ የሪፈራል ሆስፒታል ግንባታም ተጀምሯል። ከተማ አሥተዳደሩ አስፈላጊውን እገዛም ያደርጋል ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ ችግርን የሚፈቱ፣ የሕዝብን ጥያቄ የሚመልሱ እና ልማትን የሚያበረታቱ መኾናቸውንም አንስተዋል። ከተመዋ እና አካባቢው ሰላም በመኾኑ ለኢንቨስትመንት ምቹ ኹኔታ መፈጠሩንም ከንቲባው አመላክተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) በደብረታቦር ከተማ በፌዴራል መንግሥት እንዲሁም በከተማ አሥተዳደሩ እና በሕዝቡ ትብብር የሚሠሩ ፕሮጀክቶች በጥራት እና በፍጥነት እየተከናወኑ መመልከታቸውን ገልጸዋል።
የዘመናት የሕዝብ ጥያቄ የነበረው የኤሌክትሪክ ሰብስቴሽን ሰፊ አካባቢ የሚሸፍን እና ለኢንቨስትመንት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።
ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ፣ የውስጥ ለውስጥ አገልግሎቶች፣ የዩኒቨርሲቲው የልማት ሥራ፣ ከተማውን ከገጠሩ የሚያገናኙ ሥራዎች እና የሞሰብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታም ልማትን የሚያፋጥን መኾኑን ጠቅሰዋል።
በግንባታ ሂደት ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ዘሪሁን ሕዝቡ በችግርም ውስጥ ኾኖ ፕሮጀክቶቹን በባለቤትነት እና በትብብር እየሠራ በመኾኑ አድንቀዋል። እነዚህን መሰል የልማት ሥራዎች በሌሎችም አካባቢዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ኀብረተሰቡ ከጸጥታ ኀይሉ ጋር በመቀናጀት የከተመውን ሰላም በማስቀጠል በኩል ላበረከተው አስተዋጽኦም ዶክተር ዘሪሁን አመሥግነዋል።
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ታህሳስ 15 ቀን 2018 ዓ/ም
