ህብረተሰቡን እያስቸገሩ ያሉትን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከል የሚቻለው የአካል ብቃት ስፖርትን አዘውትሮ በመስራት በመሆኑ ማህበረሰቡ ስፖርቱን የእለት ከእለት እንቅስቃሴው አካል ሊያደርግ እንደሚገባም አሰልጣኞች አስገንዝበዋል፡፡

በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ከታህሳስ 10 ጀምሮ ለዩኒቨርሲቲው ስፖርት ሳይንስ ተመራቂ ተማሪዎች እና ከየወረዳው ተመልምለው ለመጡ የስፖርት ሳይንስ መምህራን እንዲሁም ለሚመለከታቸው አካላት ለ15 ቀናት የአካል ብቃት አሰልጣኞች ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ስልጠናው በንድፈ ሀሳብ እና በተግባር ሲሰጣቸው በመቆየቱ ጥሩ እውቀት እና ክህሎት ማግኘታቸውን ሰልጣኞች ተናግረዋል፡፡
በስልጠናው ላይ ሲሳተፉ ከቆዩት የዩኒቨርሲቲው ስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች መካከል ተማሪ አድዋ ካሳ እና ከወረዳዎች መጥተው ስልጠና ከወሰዱት መንግስት ሰራተኞች መካከል አቶ ሰለሞን ሲሳይ በሰጡን አስተያየት በቆይታቸው የንድፈ ሀሳብ እና የተግባር ስልጠና መውሰዳቸውን ገልፀው ከስልጠናው ጥሩ እውቀት እና ክህሎት በማግኘታቸው በተለምዶ ይሰሩት የነበረውን የአካል ብቃት ስፖርት በዘመናዊ መንገድ ለመስራት እንደሚያስችላቸው አንስተው በቀጣይም ሌሎችን በጥሩ መንገድ ለማሰልጠን ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀዋል፡፡
በርካታ ወገኖች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች በመጠቃት ለተለያየ ችግር እየተጋለጡ መሆናቸውንም ጠቅሰው የአካል ብቃት ስፖርት እነዚህን በሽታዎች ለመከላከል እና ጤናን ለመጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ማህበረሰቡ የአካል ብቃት ስፖርትን በማዘውተር በሽታዎችን መከላከል እና ጤናውን መጠበቅ እንዳለበትም መክረዋል፡፡
በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር እና የአካል ብቃት ስፖርቱ አሰልጣኝ የሆኑት መምህር ምትኩ አርእያው እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ባሉት አመታትም ለስፖርት ሳይንስ ተመራቂ ተማሪዎች እና ለሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት የአካል ብቃት ስፖርት ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው በዚህ አመትም በተመሳሳይ መልኩ ስልጠና መሰጠቱን እና ስልጠናውን በጥሩ መንገድ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
የአካል ብቃት ስፖርት ህብረተሰቡን እያስቸገሩ ያሉትን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን እና ጤናን ለመጠበቅም የሚያስችል መሆኑን ገልፀው ህብረተሰቡም የአካል ብቃት ስፖርቱን የእለት ከእለት እንቅስቃሴው አካል በማድረግ አዘውትሮ መስራት እንዳለበት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የስፖርት ቡድን መሪ አቶ ጋሸው ባይነስ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ሲሰጥ የቆየው አካል ብቃት ስፖርት አሰልጣኞች ስልጠና በተለምዶ ይሰራ የነበረውን በሳይንሳዊ ዘዴ ለመስራት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልፀው ከተማ አስተዳደሩም ሰልጣኞችን ልኮ ስልጠናውን እንዲወስዱ አድርጓል ብለዋል፡፡
የአካል ብቃት ስፖርቱ በትምህርት ቤቶች በአግባቡ እንዲሰጥ ለማድረግ እና ሌላውም የማህበረሰብ ክፍል ስፖርቱን አዘውትሮ እንዲሰራ ለማድረግ በትኩረት ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም አንስተው የአካል ብቃት ስፖርት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው በመሆኑ ሁላችንም ስፖርቱን ማዘውተር አለብን ብለዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ታህሳስ 23 ቀን 2018 ዓ.ም
