የከተማ አስተዳደሩ አስተባባሪዎች እና ሌሎችም የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት በተገኙበት ስልጠናቸውን ሲወስዱ የቆዩት ምርጥ 150 ሚሊሻዎች ተመርቀዋል፡፡

በምርቃ መርሀ ግብሩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ሚሊሻ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ብሩክ አለምነው እንዳሉት የውስጥና የውጭ ጠላቶች እየሰሩት ባለው እኩይ ተግባር በባለፉት ቅርብ አመታት በክልላችን በተፈጠረው ግጭትና የሰላም እጦት በርካታ ጉዳቶች እየደረሱ መሆናቸውን አንስተው የፀጥታ ሀይሉ በሰረው ስራ ሰላሙ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመው ያለውን ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገርና የህዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ የተመረቁ ሚሊሻዎች በትኩረት ይዘው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን እና ትልቅ ትርጉም ያለው የህዳሴው ግድብ በመንግስትና በህዝብ ትብብር ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግልግሎት መብቃቱን ገልፀው ይህም የታሪካዊ ጠላቶቻችን ሴራ ያከሸፈ እና ለዘመናት የቆየውን ቀይ ባህርንና አሰብ ወደብን የመጠቀም ፍላጎት ከፍ ያደረገ መሆኑን ተናግረው ቀይ ባይርንና አሰብ ወደብን የመጠቀም መብት አለንም ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ሀላፊ ኮማንደር አብራራው አበጀ በበኩላቸው እንዳሉት የሚሊሻ ሀይሉ ለመንግስትና ለህዝብ ታማኝ በመሆን ወታደራዊ ስነምግባርን ተላብሶ እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮች በአላማ ጽናት በማለፍ የተሰጠውን ተልእኮ እየፈፀመ እንደሚገኝ እና በቀጣይም አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት አስገንዝበው የፀጥታ ሀይሉ በሰራው ስራ የተሻለ ሰላም እንዲኖር ማድረግ መቻሉን ገልፀው ያለውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ በቁርጠኝነትና በትጋት መስራት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
በተያዘው አመት ለ2ኛ ዙር ምርጥ 150 ሚሊሻዎች እየተመረቁ መሆናቸውንም ጠቁመው ተመራቂ ሚሊሻዎች የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠናዎች መውሰዳቸውን ገልፀው ስልጠናው ለነገ ስንቅ የሚሆን በመሆኑ ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በተገቢው ሁኔታ ተጠቅመው የሚሰጡ ተልእኮዎችን በአግባቡ መፈፀም እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
በምርቃ መርሀ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ደረጉት የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀይለኢየሱ ሰለሞን ሀገራችን ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር መሆኗን አንስተው የውስጥና የውጭ ጠላቶች ሀገራችን ለማሳነስ ተንኮል እየሰሩ ቢሆንም መቸም ቢሆን እንደማይሳካላቸው ተናግረው ለዚህ ደግሞ በየዘመኑ መስዋትነት እየከፈሉ ሀገራችን ያስከበሩ ጀግኖች ባለውለታ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በህዝቡ ትብብር ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው ዳግማዊ አድዋ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረ እና ለሌሎችም ፕሮጀክቶች መሰረት የጣለ መሆኑን አንስተው የአማራ ህዝብ ጥያቄን ሽፋን አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለው ታጣቂ ሀይል መጠነ ሰፊ ጉዳት ማድረሱን ጠቅሰው የፀጥታ ሀይሉ በሰራው ስራ ሰላሙ ላይ መሻሻል መምጣቱን እና ምሩቃን ሚሊሻችም ሰላምን ለማጽናትና የማህበረሰቡን ደህንነት ለማረጋገጥ ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ከተመራቂ ሚሊሻዎች መካከል ሀሳባቸውን የሰጡን ሚሊሻዎች እንዳሉት ከስልጠናው ጥሩ እውቀትና ክህሎት ማግኘታቸውን ገልፀው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በአግባቡ ተጠቅመው የሚሰጣቸውን ተልእኮ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙት ሶስቱ ክፍለ ከተሞች የተመረቁት ምርጥ 150 ሚሊሻዎችም የጎዳና ላይ ትርኢት አሳይተዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ታህሳስ 12 ቀን 2018 ዓ/ም
