በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት አስተባባሪነት በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሰውን የሀይል ጥቃት ለመከላከል በ1ኛው እና በ2ኛው ሩብ አመት ላይ የተሰሩትን ስራዎች ከባለድርሻና ከአጋር አካላት ጋር በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በመድረኩ ላይ በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት የሴቶችና ህጻናት ፎካል አቶ ፍስሀ አስማረ በ1ኛው እና በ2ኛው ሩብ አመት የተከናዎኑትን ተግባራት ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ሴቶችና ህጻናት መብታቸው እንዲከበር እና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አንስተው በእነዚሁ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርሰው የሀይል ጥቃት እየጨመረ ያለበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው ድርጊቱን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን እና ተፈጽሞ ሲገኝም አጥፊዎች ተገቢውን ህቃዊ ቅጣት እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሴቶችና ህጸናት ላይ አስገድዶ መደፈር፣ እገታ፣ ግብረ ሰዶም፣ ድብደባና ሌሎችም ወንጀሎች እየተፈፀሙ መሆናቸውን ጠቅሰው ድርጊቱን ለማስቆም ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበው ባለድርሻና አጋር አካላት ተቀናጅተንና ተባብረን መስራት አለብንም ብለዋል፡፡
አቶ ፍስሀ አያይዘውም ለችግር ተጋላጭ ወገኖች የገንዘብ፣ የአልባሳት፣ የምግብ፣ የትምህርት መሳሪያ ቁሳቁስ እና ሌሎችም ድጋፎች መደረጋቸውን ገልፀው በተለያየ አግባብ ችግር ላይ የሚገኙ ወገኖችን ማገዝና መደገፍ አለብንም ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላትም በሰጡት ሀሳብ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን አንስተው ድርጊቱን ለማስቆም ለማህበረሰቡ በአግባቡ ግንዛቤ መፍጠር፣ ስራዎችን በቅንጅት መስራት እና በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ ህጋዊ ቅጣት መወሰድ እንዳለበት ገልፀዋል፡፡
በሚነገርበት ልክ ተግባራትን በመፈፀም ረገድ ክፍተት ያለ በመሆኑ ባለድርሻና አጋር አካላት በትኩረት ይዘው ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረው ጉዳዩ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የደረሰ በመሆኑ ከችግሩ ለመውጣት ሁላችንም በባለቤትነት ይዘን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
በመድረኩ ተሳታፊዎች ለተነሱት የተለያዩ ሀሳቦችም በአቶ ፍስሀ አስማረ እና በሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት መልስና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሀብተማርያም አለማየሁ እንደገለጹት በሴቶችና ህጻናት ላይ እየተፈፀመ ያለው የሀይል ጥቃት እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ በመኖሩ ድርጊቱን ለመከላከል በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበው በየደረጃው ያለው የሴቶች አደረጃጀትም ማገዝ አለበት ብለዋል፡፡
በአጥፊዎች ላይ እየተወሰደ ያለው ህጋዊ ቅጣት አስተማሪ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራም ጠቁመው ለማህበረሰቡ የንቃተ ህግ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ እና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረው የሴቶችንና ህጻናትን ደህንነት ለማስጠበቅ ሁላችንም ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ቄስ መልካሙ ላቀው እንደተናገሩት በሴቶችና ህጻናት ላይ እየደረሰ ያለው የሀይል ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ ከችግሩ ለመውጣት በትኩረት ይዞ መስራት እንደሚያስፈልግ አንስተው ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተውና ተናበው መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
ሴቶችና ህጻናት ለሁሉም ጉዳይ አስፈላጊ በመሆናቸው እነሱን መንከባከብና መጠበቅ እንደሚገባ ጠቁመው እየተፈፀመ ያለውን ከእሴት የወጣ ድርጊት ሁላችንም ማውገዝና መከላከል አለብን ብለዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ታህሳስ 11 ቀን 2018 ዓ/ም
