የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የ2017 ዓ/ም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አፈጻፀም ግምገማ እና የ2018 በጀት አመት እቅድ ትውውቅ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል፡፡



በንቅናቄ መድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን እንዳሉት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ለህብረተሰቡ ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት እንደሚገኝ አንስተው እንደ ከተማ አስተዳደር የጤና መድን ስራ አፈጻፀም ከአመት ወደ አመት እየተሻሻለ መምጣቱን ገልፀው የዚህን አመት የጤና መድን ተግባርም በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት ይዞ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የጤና መድንን እና ሌሎችንም ስራዎች አቀናጅቶ መፈፀም እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ከተለመደው አሰራር በመውጣት ተግባራትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናዎን ጥረት ማድረግ አለብንም ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ሀብት አሰባሰብና አጋርነት ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ፍቃዴ ያለው በ2017 ዓ/ም የነበረውን እቅድ አፈጻፀም ሪፖርት እና የዚህን አመት እቅድ አቅርበዋል፡፡ በባለፈው አመት 18 ሽህ 300 አባውራዎችን/እማውራዎችን በከፋይና መክፈል በማይችሉ የጤና መድን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀው ከ43 ሚሊየን ብር በላይ በማሰባሰብ ከ39 ሚሊየን ብር በላይ ለአገልግሎት መዋሉን እና ከ4 ሚሊየን ብር በላይ ደግሞ ወደ ዚህ አመት በማዞር አገልግሎት እየሰጠበት መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
በተያዘው አመት 21 ሽህ 990 አባውራዎችን/እማውራዎችን በከፋይና መክፈል በማይችሉ የጤና መድን ተጠቃሚ ለማድረግ በእቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመው ከ34 ሚሊየን ብር በላይ በማሰባሰብ ለማህበረሰቡ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል፡፡ የዚህን አመት የጤና መድን ተግባር ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማጠናቀቅ ሁላችንም በባለቤትነት ይዘን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላትም በሰጡት ሀሳብ ማህበረሰቡ ለጤና መድን ያለው አመለካከትና አስተሳሰብ እያደገ የመጣበት ሁኔታ በመኖሩ ተግባሩን በሚፈለገው መንገድ በመፈጸም በተያዘው ጊዜ እንደሚያጠናቅቁ ገልፀው ከጤና መድን እድሳቱ ጎን ለጎን የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል፡፡
በጤና ተቋማት ለህብረተሰቡ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን አንስተው አሁንም የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ያለባቸውን የስራ ክፍሎች ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ተናግረው መድሀኒት በበቂ ሁኔታ መቅረብ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ በረከት ገደፈው እንዳሉት በባለፈው አመት ብዙ የማህበረሰብ ክፍሎችን የጤና መድን አባል በማድረግ በርካታ ወገኖች የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ገልፀው በዚህ አመትም የጤና መድን ተግባርን ውጤታማ በማድረግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበው የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻሉን እና የመድሀኒት አቅርቦቱም ማደጉን ተናግረዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ደበበ አክሎግ እንደገለጹት የጤና መድን አገልግሎት ለማህበረሰቡ ትልቅ ጥቅም እየሰጠ በመሆኑ የጤና መድን ተግባርን ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበው ህብረተሰቡን በአግባቡ ማዳረስ እና በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ስራዎቻችን አቀናጅተን መስራት አለብንም ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀይለኢየሱስ ሰለሞን በበኩላቸው የባለፈው አመት የጤና መድን ስራን በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉን አስታውሰው የዚህን አመት የጤና መድን ስራም ውጤታማ በሆነ መንገድ በመፈፀም በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት ይዞ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበው በጤና ተቋማት ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመድሀኒት አቅርቦት የተሻለ በመሆኑ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ታህሳስ 04 ቀን 2018 ዓ/ም
