ደብረታቦር ከተማ በ14ኛው ክፍለ ዘመን በ1327 ዓ/ም በአፄ ሰይፈ አርዕድ እንደተመሰረተች የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ተስማሚ የአየር ንብረትን ከጣና እና ከጉና አዋህዳ የምትመግብ ሲሆን በዚህም ለብዙ ዘመናት የሀገሪቱ ማእከል በመሆን አገልግላለች፡፡
ደብረታቦር የብዙ ነገስታቶች መዲና የነበረች ከተማ መሆኗን አሁንም ድረስ የሚገኙት የቤተ-መንግስታት ፍርስራሾች ምስክር ናቸው፡፡ በአራቱም አቅጣጫ በንግስናቸው ጊዜ ታሪክ የሰሩ ጀግና አባቶቻችን መቀመጫ በነበሩ ታሪካዊ ቦታዎች ተከባ የምትገኝ ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማ ናት፡፡
ለአብነት ያህል የአጼ ሱሲኒዮስ አሪንጎ ቤተ-መንግስት፣ የአጼ ሰርፀ ድንግል ማህደረ ማርያም ቤተ-መንግስት፣ የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ አንገት እዳ ቤተ-መንግስት እና የአጼ ዮሀንስ 4ኛ ሰመርንሀ ቤተ-መንግስት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡


ከተማዋ የብዙ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ የመስብ ሀብቶች ባለቤት ስትሆን በኢትዮጵያ ብቸኛው የዜማ ማስመስከሪያ ትምህርት ቤት የሆነው ተክሌ አቋቋም የሚገኘው በዚችው የታደለች ከተማ ነው፡፡ ለሀገራችን ባለውለታ የሆኑት ብርሀን ዘ-ኢትዮጵያ እቴጌ ጥይቱ ብጡል የተወለዱባትና ቁምነገርን የተማሩባት ከተማም ናት፡፡
ደብረታቦር ስያሜዋ በፀናበት ኢየሱስ ተራራ ላይ ሁነው 360 ድግሪ እየተዟዟሩ ቢመለከቱ ከላይ የአፍሪካ የውሀ ማማ፣ የብዝሀ ህይወት መገኛ እና የጀግኖች መብቀያ የሆነውን ጉና ተራራን፤ ከታች ጣናን በግራና በቀኝ የጣና ገባሮችን ርብና ጉማራ ወንዞችን ይመለከታሉ፡፡
ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ለቴክኖሎጅ የነበራቸውን ፍላጎት ወደ ተግባር ለመቀየር ጋፋት ላይ ብረት አስቀልጠው በአፍሪካ የመጀመሪያውን የሴባስቶፖል መድፍ ያሰሩባት ከተማም ናት፡፡ ይህም በአፍሪካ የመጀመሪያው ኢንዱስትሪ የነበራት መሆኗን ያመለክታል፡፡
ደብረታቦር ከታሪካዊ ሀብቶቿ በተጨማሪ የውብ ባህል ባለቤት የሆነች ከተማ ናት፡፡ ከተመዋና አካባቢው በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ የቱሪስት መስህብም የታደሉ ናቸው፡፡ በበርካታ ቅርስ የተሞላው ርእሰ አድባራት ደብረታቦር ኢየሱስ ቤተ-ክርስቲያንን ጨምሮ ሌሎችም መስህቦች በከተመዋ ይገኛሉ፡፡
ቱባ ባህል፣ ብዙ ታሪክ፣ ውብ ተፈጥሮ፣ ጀግና እና ሀገር ወዳድ ህዝብ የሚኖርባት ደብረታቦር አየር ንብረቷ ጥሩ በመሆኑ እና መሰረተ ልማቶች የተሟሉላት በመሆኗ ለኑሮ ተስማሚ እና ኢንቨስት ቢያደርጉ የሚያተርፉባት ከተማ ናት፡፡
ከተመዋ ከባለፉት ሁለት አስርት አመታት ወዲህ በብዙ መልኩ በለውጥና በመነቃቃት ላይ ትገኛለች፡፡ ይሁን እንጅ ከሌሎች አቻ ከተሞች ጋር ስትነጻፀር አሁንም በብዙ መንገድ መሻሻልና መለወጥ ያለባት ከተማ ነች፡፡
በደብረታቦር የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ ሲሆን አሁንም በርካታ የመልማትና የማደግ ጥያቄዎች ያሏት ከተማ ናት፡፡ ለእነዚህ የልማትና የእድገት ጥያቄዎች መፍትሄ ለመስጠት የሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል አካላት በትኩረት ይዘው ሊሰሩ ይገባል፡፡
በከተመዋ የሰላም፣ የልማት፣ የኢኮኖሚያዊ፣ የማህበራዊና ሌሎችም ስራዎች ላይ ሁላችንም የየበኩላችን አስተዋጽኦ ማበርከት የሚጠበቅብን በመሆኑ የየራሳችን አስተዋጽኦ ማድረግና በጋራ መስራት አለብን እንላለን፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ታህሳስ 06 ቀን 2018 ዓ/ም
ለተጨማሪ መረጃዎችን በሌሎች የሚዲያ አማራጮች ይመልከቱ!
ቴሌግራም ቻናል ፡- https://t.me/dtcommunication
