በአልማ አማካኝነት በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር እየሰራ ያለው የብቁ ወጣት ፕሮግራም በተለያዩ ሙያዎች እያሰለጠናቸው ያሉ ወጣቶች ምልከታ ተደረገ፡፡

አልማ ከደብረታቦር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በተለያዩ የሙያ መስኮች የአጭር ጊዜ ስልጠና እየወሰዱ ያሉትን ወጣቶች የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር አስተባባሪዎች፣ የክፍለ ከተማ ስራ አስፈጻሚዎች፣ የአልማ ልማት ማህበር ደቡብ ጎንደር ቅርንጫፍ የስራ ሀላፊዎችና ሌሎችም የሚመለከታቸው የከተማ አስተዳደሩ የስራ ሀላፊዎች ምልከታ አድርገዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ በውሀ መስመር ዝርጋታና ጥገና እንዲሁም በልብስ ስፌት ሙያዎች ላይ የአጭር ጊዜ ስልጠና እየወሰዱ ያሉ ወጣቶች ያሉበት ሁኔታ ምልከታ ተደርጓል፡፡
የደብረታቦር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የትምህርትና ስልጠና ምክትል ዲን ወ/ሪት የዝና በዛ እንደተናገሩት ሰልጣኝ ወጣቶቹ በክህሎት በቅተው ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ በትኩረት ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው ለስልጠናው የሚያስፈልጉ ግብአቶችን በማሟላት ስልጠናው እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
ጥሩ አሰልጣኞች ተመልምለው ለወጣቶቹ ስልጠናውን እየሰጡ መሆናቸውንም አንስተው ሰልጣኞቹም እየተሰጣቸው ያለውን ስልጠና በአግባቡ እየተከታተሉ ናቸው ብለዋል፡፡
ከሰልጣኞቹ ወጣቶች መካከል ሀሳባቸውን የሰጡ ወጣቶች እንዳሉት ስልጠናው በጥሩ ሁኔታ እየተሰጣቸው መሆኑን ተናግረው ጥሩ እውቀትና ክህሎት ይዘው እንደሚወጡ እና በየሰለጠኑበት ሙያ ተሰማርተው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የልብስ ስፌት ስልጠናው ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ እና የተሰጣቸው ጊዜ ደግሞ ለዚህ በቂ የማይሆን በመሆኑ የስልጠና ጊዜው ሊጨመርላቸው እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
የአልማ ልማት ማህበር ደቡብ ጎንደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዳሬክተር አቶ ወርቁ መርሻ እንዳሉት በርካታ ወጣቶችን በተለያዩ የሙያ መስኮች አሰልጥኖ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን እና ለጊዜው 139 ወጣቶችን አሰልጥኖ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በአሁኑ ጊዜ 20 ወጣቶች በውሀ መስመር ዝርጋታና ጥገና እንዲሁም 37 ወጣቶች ደግሞ በልብስ ስፌት ሙያ ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸውን እና ለሌሎቹ ወጣቶችም በቀጣይ ስልጠናዎቹ እንደሚሰጡ ገልፀዋል፡፡
ስልጠና እየወሰዱ ያሉት ወጣቶች ስልጠናውን በአግባቡ መውሰድ እንዳለባቸውም አስገንዝበው ስልጠናው በሚፈለገው መንገድ እንዲቀጥል ለማድረግ ከኮሌጁ ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ ተናግረው አልማን አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁላችንም አስተዋጽኦ ማበርከት አለብን ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን እንደተናገሩት አልማ ከኮሌጁ ጋር በመተባበር ለወጣቶቹ የሙያ ስልጠና እየሰጠ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን አንስተው ወጣቶች ስልጠናውን በተገቢው ሁኔታ በመውሰድ ብቃት ያላቸው ሁነው ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበው ከስራ አጥነት በመውጣት ራሳችሁንና አካባቢያችሁን መቀየር አለባችሁም ብለዋል፡፡
የልማት ማህበሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰው ለማህበሩ የሚሆን ገቢ በአግባቡ ለማሰባሰብ በትኩረት ይዞ መስራት እንደሚገባ አሳስበው ሁላችንም በባለቤትነት ይዘን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
በተያያዘም አልማ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር በየትምህርት ቤቶቹ እየሰራቸው ያሉት የመማሪያ ህንጻዎች ግንባታ ያሉበት ሁኔታ ምልከታ የተደረገ ሲሆን የተጀመሩት ግንባታዎች በጊዜ እንዲጠናቀቁ እና ሌሎችም ግንባታዎች እንዲሰሩ ለማድረግ ማህበረሰቡን በማስተባበር ለልማት ማህበሩ የሚሆን ገንዘብ ማሰባሰብ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ታህሳስ 01 ቀን 2018 ዓ/ም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top