የደብረታቦ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የ2018 በጀት አመት የበጋ መስኖ ስራ አፈጻፀም ግምገማ እና የ2018 በጀት አመት የተፈጥሮ ሀብት ስራ ንቅናቄ መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የደብረታቦ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ጌታቸው ይበልጣል በተያዘው በጀት አመት እየተሰራ ያለውን የበጋ መስኖ ልማት እንቅስቃሴ አስመልክተው እስካሁን ያለውን የእቅድ አፈጻፀም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ለመስኖ ልማት ምቹ ሁኔታ ያለ መሆኑን ጠቁመው በአንደኛና በሁለተኛ ዙር የበጋ መስኖ ልማት ስራ መጠነ ሰፊ ሄክታር መሬትን ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አንስተው የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎች እንዲለሙ እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ከተማ አስተዳደር በ500 ሄክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴን ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን እና እስከ ትናንት ድረስ 122 ሄክታር መሬት በስንዴ መሸፈኑን ገልፀው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በሚፈለገው መንገድ ለማስኬድ በትኩረት ይዞ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ሀላፊው የ2018 ዓ/ም የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ እቅድንም ያቀረቡ ሲሆን በከተማ አስተዳደሩ የባለፈው አመትን የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ በጥሩ መንገድ መፈፀም መቻሉን አስታውሰው በዚህ አመትም ባደገ ደረጃ ለማከናዎን ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን ብለዋል፡፡ በ17ቱ ተፋሰሶች ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመው 439.04 ሄክታር የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ እንደሚሰራ፣ 50 ሄክታር የተራራና የተራቆተ መሬትን ከልሎ እንዲያገግም ማድረግ፣ 1 ሽህ 011.39 ሄክታር ነባር የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ እንደሚሰራ፣ 152.5 ሄክታር ጥምር ደንና እርሻ ልማት ስራ መስራት፣ 838.14 ሄክታር መሬትን በስነ-ህይዎታዊ ዘዴ መሸፈን እና ሌሎችም ስራዎች እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ የአፈር ለምነትን በመጨመር የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ስራውን በአግባቡ ለማስኬድ ሁሉም አካል በባለቤትነት ይዞ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበው የዚህ አመት የተፈጥሮ ሀብት ስራ ጥር 01 የሚጀመር በመሆኑ ተግባሩን በሚፈለገው መንገድ ለመፈፀም ከአሁኑ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላትም በሰጡት ሀሳብ የበጋ መስኖ ልማትን በጥሩ መንገድ ለማስኬድ እየሰሩ መሆናቸው አንስተው የበጋ መስኖ ስንዴን በሚፈለገው አግባብ ለመፈፀም በትኩረት ይዘው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረው ስንዴና የጓሮ አትክልት በክላስተር እንዲለማ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የባለፈው አመት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ በተሻለ መንገድ እንዲሰራ መደረጉን አውስተው የዚህን አመት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራም በላቀ ሁኔታ ለመስራት ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረው በተፈጥሮ ሀብት ስራው የሚሰሩትን ስራዎች ዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመው ተግባራትን ተቀናጅተንና ተጋግዘን መፈፀም አለብንም ብለዋል፡፡
በመድረኩ ተሳታፊዎች ለተነሱት የተለያዩ ሀሳቦችም የደብረታቦ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ጌታቸው ይበልጣል መልስና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ራስን ለመቻል ግብርናውን ማዘመን፣ አዳዲስ ቴክኖሎጅን ማላመድ፣ ከተለመደው አሰራር በመውጣት ዘመናዊ አሰራርን መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው በበጋ መስኖ ልማት ስራው ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀይለኢየሱስ ሰለሞን እንደተናገሩት እንደ ሀገር የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በጥሩ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን አንስተው በከተማ አስተዳደሩም የስንዴ ልማትን በክላስተር በማልማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት ይዞ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው ተግባሩን በላቀ ደረጃ ለመፈፀም ቁርጠኛ ሁኖ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
የ2017 ዓ/ም የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ በጥሩ ሁኔታ መሰራቱን አውስተው የዚህን አመት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራም ባደገ አግባብ ለመስራት ከወዲሁ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስገንዝበው ስራውን በተነሳሽነትና በትጋት ማስኬድ አለብንም ብለዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ህዳር 26 ቀን 2018 ዓ/ም
