ዘርፈ ብዙ ጉዳት እያስከተለ ያለውን ሙስና እና ብልሹ አሰራር ለመከላከል በጋራ መስራት እንደሚገባ ተመላከተ፡፡

በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር በአለም ለ22ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ21ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍን የፀረ-ሙስና ቀን አስመልክቶ “ትውልድን በስነ-ምግባር ተቋምን በአሰራር እንገንባ” በሚል መሪ ሀሳብ ከጠቅላላ አመራሩና መንግስት ሰራተኛው ጋር የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ስነ-ምግባር መኮንን አቶ ይመኑ አለኸኝ የስነ-ምግባር ግንባታን፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራር እያደረሰ ያለውን ጉዳት፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል መሰራት ያለባቸውን ስራዎች እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክተው ለፓናል ውይይቱ መነሻ የሚሆን ሰነድ አቅርበዋል፡፡ ስነ-ምግባር ካለ ከራስ ባለፈ ለህዝብና ለሀገር ማሰብና መቆርቆር እንደሚኖር ጠቁመው ባጋጠመው የስነ-ምግባር ዝቅጠት እና የሞራል እሴቶች መሸርሸር ሙስና እና ብልሹ አሰራር እየተበራከተ መምጣቱን አንስተው ወንጀሉ ዘርፈ ብዙ ጉዳትን እያደረሰ በመሆኑ ለመከላከል በጋራ መስራት አለብን ብለዋል፡፡መልካም ስነ-ምግባርን መገንባት፣ የሙስና ወንጀልም መከላከል፣ መልካም አስተዳደርን ማስፈንና ሰላምን ማረጋገጥ አማራጭ የሌለው ግዴታ መሆኑንም አስገንዝበው የተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች መልካም ስነ-ምግባርን መገንባት፣ ቀልጣፋና ፍትሀዊ አገልግሎት መስጠት፣ ቴክኖሎጅን በመጠቀም አሰራርን ማዘመን፣ የግልፀኝነትና የተጠያቂነት አሰራርን ማስፈን፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን መከላከል እንዳለባቸው ጠቁመው እየተፈፀመ ያለውን ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ለማስቆም ሁላችንም ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡አቶ ይመኑ አያይዘውም እንደ ከተማ አስተዳደር ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አንስተው የግንዛቤ ፈጠራ ስራ፣ የሙስና ወንጀልን ቀድሞ መከላከል፣ የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ እና ሌሎችም ስራዎች እየተሰሩ በመሆናቸው በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀው ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በቅንጅት መስራት አለብን ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ አካላትም በሰጡት ሀሳብ ትውልዱን በእሴት እና በስነ-ምግባር ለመገንባት መንግስትና ማህበረሰቡ በትኩረት ይዘው ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመው ለህብረተሰቡ በተለያየ መንገድ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረው የግልፀኝነትና የተጠያቂነት አሰራርንም ማስፈን ይገባል ብለዋል፡፡
ሙስና እና ብልሹ አሰራር በስፋት ከሚታይባቸው ተቋማት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚያስፈልግም አንስተው ውስብስብ አራርን በማስቀረት ቀላል አሰራርን መከተል እንደሚገባ እና በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ገልፀው ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን በጋራ ሁነን መታገል አለብንም ብለዋል፡፡በውይይቱ ተሳታፊዎች ለተነሱት የተለያዩ ሀሳቦችም የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ስነ-ምግባር መኮንን አቶ ይመኑ አለኸኝ መልስና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ደበበ አክሎግ እንደገለጹት የስነ-ምግባር ስብራት እና የእሴት መሸርሸር በማጋጠሙ ምክንያት አግባብ ያልሆኑ ድርጊቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን አንስተው እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮች ለመሻገር ስነ-ምግባር ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን ብለዋል፡፡ሙስና እና ብልሹ አሰራር ከተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚታይ መሆኑን ጠቁመው ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት በማስተካከል እና አሰራርን በማዘመን ቀልጣፋና ፍትሀዊ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀይለኢየሱስ ሰለሞን እንደተናገሩት ሙስና እና ብልሹ አሰራር ሀገርን የሚጎዳ እና ትውልድን የሚያመክን በመሆኑ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን የሚጠየፍ ትውልድን ለመገንባት ከታች ጀምረን መስራት አለብን ብለዋል፡፡ድርጊቱን ለመከላከል የግንዛቤ ፈጠራ ስራን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም አስገንዝበው የትምህርት ተቋማት እና የሐይማኖት ተቋማት በአግባቡ ሊያስተምሩ እንደሚገባ ጠቁመው የተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎችም ስነ-ምግባርን ተላብሰው ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
 
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ/ም

Add Your Heading Text Here

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top