ከደብረታቦር ከተማ አስተዳደር የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ!

ከደብረታቦር ከተማ አስተዳደር የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ!

ከተማችን ደብረታቦር የብዙ ታሪክ፣እሴትና ባህል የሚገኝባት በሀገር ግንባታ ታሪክም ለኢትዮጵያ መጽናት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አያሌ ጀግኖችን ያበቀለችና በጽናት ለሀገር ህልውና እና ለሀገረ መንግስት ብዙ አበርክቶ ጀግኖች የበቀሉባት ከተማ ናት።

በታሪክ አጋጣሚ ለኢትዮጵያ ሀገራችን የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶች ከፊት የምትሰለፍ ባለታሪክ ከተማ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በልማት እንቅስቃሴ ወደተሻለ ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ የምትገኝ ቢሆንም በክልሉ አጋጥሞ በቆየው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በሚፈለገው አግባብ ለማስኬድ ከባድ ሁኖ ቆይቷል።

የክልሉ መንግስትም ሆነ የፌዴራሉ መንግስት በአማራ ህዝብ ጉዳይ ጥያቄ አለኝ የሚል አካል ካለ ለመወያዬትና ለመደራደር በሩ ክፍት መሆኑን በተደጋጋሚ እየገለጸ ቢገኝም ከስህተታቸው መማር ያቃታቸውና የህዝብ መከራና ችግር በማይገዳቸው አካላት በደብረታቦር ከተማ ዙሪያ በመሰባሰብ ትንኮሳ ለማድረግና ህዝብን ለማሸበር ተሞክሯል።

ከትላንት ባለመማር ህዝብን ለማሸበር፣ህጻናትን ለማስለቀስ አልፎም ሀብትና ንብረት እንዲወድም ለማድረግ አለፍ ሲልም የግል ጥቅማቸውን ከተማን እንዲወድም በማድረግ ለማሳካት ጥረት አድርገው ነበር።ዳሩ ግን ህዝቡ ለሰላም ያለውን ጽኑ ፍላጎት በተደጋጋሚ ውይይቶች በማረጋገጡና የሰላሙ ባለቤት በመሆኑ ምክንያት እቅዳቸው በቀላሉ ሊከሽፍ ችሏል።ከተማን ለማውደምና ህዝብን ለማሸበር የመጣው ቡድንም በሀገር መከላከያ ሰራዊት፣በክልሉ የጸጥታ ሀይልና በከተማው የጸጥታ መዋቅር ተመቶ ተመልሷል።

ከተማን በማውደም እና እታገልለታለሁ የሚሉትን ህዝብ በማሸበር ሊመለስ የሚችል ጥያቄ ከቶውንም ሊኖር አይችልም።

ስለሆንም የጥፋት መንገድ የቱንም ያህል እርቀት የማያስጉዝ በመሆኑ በጥፋት ተልዕኮ ተደናግራችሁ የተሰለፋችሁ አካላት ከአጥፊ መንገድ እንድትወጡና እየበደላችሁት ያለውን ህዝብ ሰቆቃ እንዲያበቃ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ጥሪ ያስተላልፋል።

በአሁኑ ሰአት ከተማዋ በፍጹም ሰላማዊ እንቅስቃሴ የምትገኝ ሲሆን ያከተማው ማህበረሰብ የተለመደ የሰላም አጋርነቱን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል እንጠይቃለን።

ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ሀምሌ 29 ቀን 2016 ዓ/ም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top