
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር በቀጣይ ወራት በሚሰሩ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ላይ ከጠቅላላ መንግስት ሰራተኛው ጋር ውይይት አደረገ!
ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ 100 ቀናት በሚሰሩ ተግባራት እቅድ ላይ ከጠቅላላ መንግስት ሰራተኛው ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ በቀጣይ 100 ቀናት የሚሰሩትን ተግባራት እቅድ ያቀረቡት የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ደበበ አክሎግ እንደገለጹት በክልላችን ሰላም እንዳይሰፍንና አለመረጋጋት እንዳይኖር ለማድረግ የሀገር ውስጥና የውጭ ጠላቶች እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው በአንድ ሁነን በመስራት የገጠመንን ችግር መሻገር አለብን ብለዋል፡፡
ችግሮች የሚፈቱት በውይይትና በምክክር መሆኑንም ተናግረው ወደ ግጭትና ጦርነት የገቡ ሀይሎች ወደ ሰላም መምጣት እንዳለባቸው አሳስበው መንግስት ሁሌም ለውይይትና ለምክክር ዝግጁ መሆኑን ገልፀው ተባብሮና ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡
ክልላችን ብሎም ከተማ አስተዳደራችን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማምጣት የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት መያዝ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበው ሰላማችን አረጋግጠን የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በጥሩ መንገድ ለማስኬድ ሁላችንም በባለቤትነት ይዘን ልንሰራ ይገባልም ብለዋል፡፡
ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ መስራት፣ በየደረጃው ያለው የመንግስት መዋቅር ተግባሩን በተገቢው ሁኔታ መፈፀም፣ መደበኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን መስራት እና ሌሎችንም ተግባራት መፈፀም በቀጣይ 100 ቀናት ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰሩ መሆናቸውን አቶ ደበበ ገልፀዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ የመንግስት ሰራተኞችም የተለያዩ ሀሳቦችን የሰጡ ሲሆን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ በከተማ አስተዳደሩ እየተሰሩ ያሉት ሁለንተናዊ ስራዎች ጥሩ በመሆናቸው አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ፣ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ሰላምን ለማምጣትና በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሁላችንም ልንሰራ ይገባል፣ በክልላችን ብሎም እንደ ሀገር እየተፈጠረ ያለውን የሰላም እጦት ችግር ለመፍታት መንግስት ከልቡ መስራትና ከታጠቁ ሀይሎች ጋር መወያዬት እንዳለበት፣ ከተመዋን በተሻለ መንገድ ለማስኬድና የልማት ስራዎችን በጥሩ ሁኔታ ለማስቀጠል አመራሩና ህዝቡ ተባብሮና ተቀናጅቶ ሊሰራ እንደሚገባ፣ የፌደራል መንግስት ለዘመናት እየቀረቡ ያሉትን የአማራ ህዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት፣ በከተመዋ እየተፈፀሙ ያሉትን የተለያዩ ወንጀሎች ለመከላከል ማህበረሰቡ በባለቤትነት ይዞ መስራትና የፀጥታ ሀይሉን ማገዝ አለበት የሚሉ እና ሌሎችንም ሀሳቦች ሰጥተዋል፡፡
በመድረኩ ተሳታፊወች ለተነሱት የተለያዩ ሀሳቦችም የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ደበበ አክሎግ መልስና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የአማራ ህዝብ ጥቄዎች በተገቢው ሁኔታ ተለይተው መፍትሄ ለመስጠት መንግስት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው አንዳንዶቹ የልማት ጥያቄዎች መልስ እያገኙ መሆናቸውን ጠቁመው ለሌሎቹ ጉዳዮችም መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
እንደ ሀገርና እንደ ክልል እየተፈጠሩ ያሉትን ችግሮች ለመፍታትም ሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ ጥቅም ያለው መሆኑን ገልፀው በምክክሩ ላይ ውጤታማ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበው ተባብረንና ተጋግዘን በመስራት እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮች መፍታት እና የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በአግባቡ መስራት አለብንም ብለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደሴ መኮንን እንደተናገሩት በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ለማድረግ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ የአማራ ህዝብና የኢትዮጵያ ጠላቶች በሴራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው አሁን ያለው ግጭትና ጦርነት የአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄወች መፍትሄ እንዳያገኙ ለማድረግ ታስቦ የሚካሄድ በመሆኑ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ይህን ተገንዝቦ ግጭቱና ጦርነቱ እንዲያበቃ ለማድረግ መስራት አለበት ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የፀጥታ ሀይል ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን እና የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል እየሰራ እንደሚገኝም ገልፀው ህብረተሰብም ተደራጅቶ አካባቢውን መጠበቅና የፀጥታ አካሉን ማገዝ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
በየተቋማቱ ለማህበረሰቡ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ችግር ያለበት በመሆኑ ተቋማት ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ከንቲባው ተጋግዘንና ተባብረን በመስራት የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በተሻለ ሁኔታ ማስኬድ አለብንም ብለዋል፡፡
ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ/ም
ተጨማሪ መረጃዎችን በሌሎች የሚዲያ አማራጮች ይመልከቱ!
ፌስ-ቡክ፡-https://www.facebook.com/profile.php?id=100064645364506
ቴሌግራም ቻናል ፡- https://t.me/dtcommunication
ትዊተር፡- https://twitter.com/debre_tabor_com
ዩቲዩብ፡- https://youtu.be/BktVrGvXms
